ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትና የቡና ወጪ ንግድን አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና የቡና ምርታማነትና ወጪ ንግድን በከፍተኛ በሁኔታ ማሳደጉን አምራቾችና ላኪዎች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ የሪፎርም ስራ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን መግለፃቸው ይታወሳል።

ይህም በዘንድሮው ዓመት ከቡና ኤክስፖርት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ማስገኘት መቻሉን መግለፃቸውም እንዲሁ።

የኦሮሚያ የቡና አቅራቢዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የከብሬ ለኬ ቡና ላኪ ድርጅት ባለቤት ፈጠነ የኋላእሸት ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበሩ የፖሊሲ ክፍተቶች በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ፈጥረው ቆይተዋል።

ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለዘርፉ ተዋናዮች መልካም እድል መፍጠሩን ጠቁመው ይህን ተከትሎም የቡና ኤክስፖርት በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍ እያለ መምጣቱን ገልጸዋል።

የተደረገው ማሻሻያ በእሴት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ችግሮችን መለየት ማስቻሉን ይህም ቡና በቀላሉ ወደ ውጭ እንዲላክ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አሰራሮች ዲጂታላይዝ መደረጋቸው ዘርፉን ዘመናዊ እንዳደረገውና ለቡና ወጪ ንግድ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ሪፎርሙን ተከትሎ በተሰሩ ስራዎች የቡና ምርታማነትና ጥራት በመጨመሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት የቡና ወጪ ንግድ በየዓመቱ በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን አብራርተዋል።

በቀጣይም መንግስትና የዘርፉ ተዋናዮች ትብብራቸውን አጠናክረው ከቀጠሉ የወጪ ንግድ አፈፃፀምንና የዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ማሽነሪና መለዋወጫ አምራቾች ማህበር ፀሀፊ እና የፅዮን ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግና ብረታ ብረት ኢንተርፕራይዝ ባለቤት ዮሃንስ ግርማ በበኩላቸው መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

በተለይም ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱና የወጪ ንግድ ኤክስፖርት ምርትን ለማሳደግ ለሚሰሩ አምራቾች ውጤታማ የሚያደርጉ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአምራች ዘርፉ በተሰጠው ትኩረትና እየተደረገ ባለው አጠቃላይ ድጋፍ የምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ማጎልበት መቻሉንም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪዎችን ችግር ከመለየት ጀምሮ በዘላቂነት ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ችግሮችን ለመፍታት የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አመላክተዋል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ ማነቆ በመፍታት ቀደም ሲል 40 ቢሊየን ብር የነበረውን የብድር መጠን ወደ 115 ቢሊየን ብር ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎቻችን ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነት፣ ትርፋማነትና የመስፋፋት ዕድል ከፍ እያለ መምጣቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም