ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ875 ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ

ሸገር፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ875 ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የከተማዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም "ተስፋን እንትከል!" በሚል መሪ ሐሳብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ ለመሥራት እንዘጋጅ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

"በእነዚህ ቀናት ውድ የሀገሬ ልጆች አስፈላጊውን ዝግጅት እንድታደርጉና በጋራ ተስፋን እንትከል" በማለትም መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

መርሃ ግብሩን አስመልክተውም የከተማው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የደረቁ ምንጮችን በማጎልበትና የአፈር ለምነትን በመመለስ ምርትና ምርታማነትን አሳድገዋል። 

በዘንድሮው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተማው በ875 ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ለሚተከሉ ችግኞች የቦታ ልየታ፣ የጉድጓድ ዝግጅት፣ እንዲሁም የማጓጓዝ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የተዘጋጁ ችግኞችም ለምግብ፣ ለከተማ ውበት፣ ለደን ሽፋንና ለሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች የሚውሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዕለቱ ለተከላው 210 ሺህ የሚጠጋ የኅብረተሰብ ክፍል በንቃት እንደሚሳተፍም አክለዋል።

ተግባሩ ለከተማዋ አረንጓዴ ልማት ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል የገለጹት ኃላፊው፤ ስኬቱን የበለጠ ለማጠናከር ከተከላው ባሻገር የእንክብካቤና ጥበቃ ሥራዎች ላይ ትኩረት መደረጉንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም