ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ንግድ ትስስርና ዕድገት ቁልፍ ሀገር ነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ንግድ ትስስርና ዕድገት ቁልፍ ሀገር ነች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች የምትገኝ ቁልፍ ሀገር መሆኗን በአፍሪካ የንግድና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው 'ትሬድ ካታሊስት አፍሪካ' ገለጸ።
ኢትዮጵያ ያሏት የታሪክ፣ የስነ-ህዝብ፣ የመሰረተ ልማት እና የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ፀጋዎች በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማፋጠን ወሳኝ ድርሻ እንድትጫወት አስችለዋታል፡፡
እንዲሁም የሃይል እና ትራንስፖርት መረቦችን ለመዘርጋትና በአህጉር ደረጃ የፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎችን ለመቀየስ የሚያስችላትን የጎላ ድርሻ ይሰጣታል።
የ'ትሬድ ካታሊስት አፍሪካ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ አደሬ አዳንኮ ኒያንጎ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር፣ ትልቅ ኢኮኖሚና በርካታ አምራች ወጣቶች ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ይህ መልካም አጋጣሚ ሀገሪቱ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንድታበረክትና ተጽዕኖዋን እንድታሰፋ የሚያስችላት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ በርካታ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፎች ለልማትና ለስኬት ሰፊ እድል ይዘው እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በተለይም በግብርና እና በግብርና ማቀነባበር መስኮች ላይ ያሉ ሰፊ ዕድሎችን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም እንደ ጤና፣ ትምህርት እና የፋይናንስ አገልግሎቶች ባሉ ቁልፍ ዘርፎችም ትልቅ የእድገት አቅም መኖሩን ጨምረው አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው ያሉት ወሳኝ ማዕድናት የኢትዮጵያን ሀገራዊ ብልጽግና በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቀጣናዊ እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች የምትገኝ ቁልፍ ሀገር ናት ብለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ የፖሊሲ እና ጥናት ተቋም (ODI) ዋና ተመራማሪ ማክሲምን ዲባራ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር በፍጥነት እያደጉ ካሉ የኢኮኖሚ ማዕከላት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያሰመዘገበች እንደምትገኝ አንስተው፤ በተለይም በግብርና እና በአምራች ዘርፎች የሚታየው የእድገት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል
ይህ እድገት ኢትዮጵያ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ከቀሪው የአፍሪካ አህጉር ጋር የሚኖራቸውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያሳልጥ ስትራቴጂካዊ መድረክ እንድትሆን እንደሚያስችላት ገልጸዋል።
እየተከናወኑ ያሉ የኢንዱስትሪና የግብርና ልማት ሥራዎችም ለሀገራቱ የምግብ ዋስትና እና የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች ተስማሚ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተመራማሪው ይህም ኢትዮጵያን አጠቃላይ አህጉራዊውን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያስተስስር ቁልፍ ማዕከል እንደሚያደርጋት አስታውቀዋል።