ቀጥታ፡

በባሌ ዞን ከበልግ እርሻ እስካሁን 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

ሮቤ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በበልግ ወቅት ከለማወ መሬት ከ6 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ በሜካናይዜሽን የታገዘው የሰብል ስብሰባ ሒደት በድህረ ምርት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።


 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አልይ መሐመድ እንዳሉት፤ በዞኑ በበልግ ወቅት ከለማው 277 ሺህ 182 ሄክታር መሬት ውሰጥ እስካሁን በተደረገ ጥረት ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል።

ይህም በሰብል ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት 90 በመቶውን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

የምርት አሰባሰብ ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉንና በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ ከለማው መሬት ስምንት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በበልግ ወቅት ከለማው መሬት 107 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ ሰብል መልማቱን ጠቁመው እስከ አሁን ከተሰበሰበው 82 ሺህ ሄክታር መሬት 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ በኮምባይነር እየተደረገ ካለው የመሰብሰብ ስራ በተጓዳኝ በጥቃቅን ማሽነሪዎችና በሰው ጉልበትም እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመካናይዜሽን ሰብልን ለመሰብሰብ የሚደረገው ጥረት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ከማስቀረቱም በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም አክለዋል።


 

በዞኑ በበልጉ ወቀት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ከተከሸፈነው ማሳ 73 በመቶ የሚሆነው የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችና ሙሉ ፓኬጆችን በመጠቀም በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሀኪም አልይ ናቸው።

በዞኑ በመኸር፣ በበልግና በመስኖ አማራጮች ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማና፣ ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ዓመታዊ ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።


 

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሐጅ ሳፊ አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ ሰብልን በኮምባይነር በመሰብሰብ ይደርስ የነበረውን ብክነት ማስቀረት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀትም በኩታገጠም አሰራር በመታገዝ መሬታቸውን ማልማታቸው ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በዝናብ ውኃ አማራጭ በመኽርና በልግ አዝመራ በዓመት ሁለቴ ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ ባሌ ዞን ነው።

በዞኑ ከሚያዝያ ወር መጨረሻ እስከ ነሐሴ መገባደጃ ያለው ጊዜ የበልግ የምርት ወቅት መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም