ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና ነው - የተለያዩ የእምነት ተቋማት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና ነው - የተለያዩ የእምነት ተቋማት አባቶች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና እንደሚሆን ተመካካሪ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በመሰባሰብ በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት እየተመካከሩ ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች፤ የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ነፃ ሆኖ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተስፋ ሰጪ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ተመካካሪዎች ማካከል መልዓከ ሕይወት አባ ወልደ ዮሐንስ ሰይፉ፤ በዚህ ምክክር ያልተወከለ ኢትዮጵያዊ የለም ብለዋል።
ምክክሩ እርስ በእርስ ይበልጥ እንድንተዋወቅ እያደረገን ነው ያሉት መልዓከ ሕይወት፣ ሂደቱ አንዱ የሌላውን ሐሳብ ሳይነቅፍ፣ ፍጹም መከባበርና መተሳሰብ በሰፈነበት ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ ሰላምና ልማት የሚፈልግ መሆኑን ከመገንዘብ ባለፈ ሰላሟ የተጠበቀ፣ አረንጓዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ወሳኝ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።
የምክክር ሂደቱ በአካታችነቱና አሳታፊነቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ተመካካሪ አብዱልመጂድ ጃፋር ናቸው።
"ይዘን የመጣነው የሀገር ኃላፊነት ነው፤ በመሆኑም ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ልማትና እድገት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ምክክር እያደረግን እንገኛለን" ሲሉም ተናግረዋል።
ለሀገር በሚበጁ ጉዳዮች ላይ ተስፋ ሰጪ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ያመላከቱት ተመካካሪው፤ በሀገራችን የጋራ መግባባት ከተፈጠረ ሌላ የሚጎድል ነገር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ሐሳባቸውንም በነጻነት መግለጻቸውን በማንሳት፣ ከዚህ ምክክር በኋላ ሀገራችን በልማት ላይ ብቻ እንድታደርግ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው፤ ለአንድ ሀገር ዘላቂ መረጋጋትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መሠረት በሚሆኑ ዐበይት ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ ሐሳብ እየተለዋወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን የሚያጎለብትና ለትውልድ የሚሻገር ሰላምን የሚገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አባ አማኑኤል ዮሴፍ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ፍጹም የመደማመጥና ቤተሰባዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያሻግሩ ሐሳቦች ተነስተው በነጻነት ምክክር እየተደረገባቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል።