ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል በመኸር እርሻ ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል 

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በተያዘው የመኸር እርሻ ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዝርዕት፣ በጥራጥሬና በስራስር ሰብሎች እንደሚለማ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ እንደገለጹት፤ በሲዳማ ክልል በተያዘው የመኸር እርሻ ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዝርዕት፣ በጥራጥሬና በስራስር ሰብሎች ይለማል።

ኃላፊው አክለውም መኸር አብቃይ ለሆኑ ወረዳዎች 183 ሺህ 410 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 47 ሺህ 458 ኩንታል ምርጥ ዘር መሰራጨቱን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በዘር ከሚሸፈነው ማሳ በጥራጥሬ፣ በብርዕና በሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች 123 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማና ቀሪው በድንች፣ በስኳር ድንችና ሌሎች የስራ ስር ሰብሎች እንደሚለማ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ማሳውን ለዘር እያዘጋጀ እንደሚገኝና በአንዳንድ ወረዳዎች የዘር መዝራት ስራ እንደተጀመረ ጠቁመዋል።

በበልግ እርሻ በዝናብ መቆራረጥ ምክንያት የጠፋ ሰብልን ለማካካስ ዘር እንደቀረበላቸውና በመኸር እርሻ ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያለሙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በክልሉ የደራራ ወረዳ አርሶ አደር ተሰማ ተስፋዬ፣ በበልግ ወቅት በበቆሎ ያለማነውን የደረሰ ሰብል በማንሳት ለመኸር እርሻ ቦሎቄና የስራ ስር ሰብል ለማልማት ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።

ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎች ዘር እንደቀረበላቸውና የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑንም አርሶ አደሩ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ታዲዮስ መልካሙ በበኩላቸው በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ በመታገዝ በመኸር የሚያለሙትን ማሳ እያዘጋጁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

በበልግ እርሻ በቆሎ በኩታ ገጠም እንዳለሙ ያነሱት አርሶ አደሩ የመኸሩንም በዚሁ የእርሻ ስነ-ዘዴ እንደሚያለሙም ገልጸዋል።

በክልሉ በመኸር እርሻ ከ430 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉና ከሚለማው 169 ሺህ ሄክታር ማሳ ከ15 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም