በሀረሪ ክልል የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 25/2018(ኢዜአ):- በ2019 በጀት ዓመት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ እንደሚሰራ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዕረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
ቢሮው በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጡን በማጎልበት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማን ለመፍጠር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደገለፁት ቢሮው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለሚያረጋግጡ ተግባራት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
በክልሉ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል 20 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
እቅዱን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግም ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል የከተማ፣ ገጠርና ሰፈር ፕላን ሽፋን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና የካዳስተር ሽፋንን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በተለይ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ የኮሪደር ልማትና የሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታን በተያዘላቸው ግዜ እንዲጠናቀቁም ይሰራል ብለዋል።
በተለይ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ በማዘመን ለዜጎች ፍትሀዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገልፀዋል።