ቀጥታ፡

ከእውነት የራቀና ለትውልድ የማይበጅ የሴራ ትንተና ውጤቱ ጥፋት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ከእውነት የራቀና ለዛሬም ሆነ ለመጪው ትውልድ የማይበጅ የሴራ ትንተና ውጤቱ ጥፋት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የኢትዮጵያ ህዝቦች የመዋሃድና አብሮ የመዝመት ታሪክ ቢኖራቸውም በዘመናት መካከል ስልጣን ሲመጣ አልጋ ሳይጸና በኃይል ስልጣን የመገዳደር ፍላጎት የሀገሪቱ ባህል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁልጊዜም በኃይል ስልጣን ለመያዝ መሞከር የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደነበር አስታውሰው ለዚህም ከልጅ እያሱ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ከለውጡ በኃላ የተከሰተውን ሙከራ በማሳየነት አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የሰኔ 15ቱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ለየት የሚያደርገው በክልልና ከተማ ደረጃ ለመፈጸም የተሞከረ መሆኑ ነውም ብለዋል፡፡

ይህም በታሪክ እንደጥቁር ጠባሳ የሚወሰድ መጥፎ ክስተት መሆኑን ጠቁመው ይህ መጥፎ ክስተት የለውጥ ኃይል የሚባሉና ቢቆዩ ለሀገር ብዙ የሚያበረክቱ ሰዎችን ያሳጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ክስተቱ ይበልጥ የሚያሳዝነው ገዳይንም ሟችንም በጀግንነት ያወሳ በመሆኑ ታሪክን እያንሻፈፉ በፈለጉት መንገድ በማቆየት ትልቅ የትርክት ስብራት የፈጠረ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ከመልካምም ከመጥፎም ታሪክ መማር ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ታሪክን እየመረጡና እያንሻፈፉ ማቆየት የነገውን ትውልድ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ታሪክም የተንሸዋረረ የፖለቲካ ትርክት ውጤት መሆኑን በመጠቆም በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ ሴራ ተንታኞች መጠቀሚያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከእውነት የራቀና ለዛሬም ሆነ ለነገ የማይበጅ የሴራ ትንተና ጥፋት እንደሚያመጣም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም