ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ ሳይሆን ሂደት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ ሳይሆን ሂደት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ ሳይሆን ሂደት በመሆኑ በዚህ ውስጥ ጉዳዮች ሊቀያየሩ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም ለውጡንና የዳያስፖራዎችን ሚና በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ለውጡን በመደገፍና ባለመደገፍ ጎራ የመቀያየር ሁኔታ በዳያስፖራዎችም ሆነ አልፎ አልፎ በሀገር ውስጥ ባሉ ግለሰቦችም ይታይ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ለዚህም ሶስት ጉዳዮችን በምክንያትነት ያነሱ ሲሆን ግለሰቦች የነበራቸው የተሳሳተ ስሌት የመጀመርያው መሆኑን ጠቁመዋል።
አንዳንድ ግለሰቦች የለውጡ ባለቤት እንደሆኑንና ለውጡ እኔ በማስበው መንገድ መሄድ አለበት የሚል እምነት ያላቸው ግለሰቦች ሃሳብ የተጋባባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ለውጡ የብዙ ሰዎች ጥረትና በርካቶች ዋጋ የከፈሉበት በመሆኑ በማስተባበር የሚመራ እንጂ የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈጸም አለመሆኑን ሲረዱ የጎራ ለውጥ የሚያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ለርካሽ ዓላማ የሚቃወሙ ግለሰቦች መኖራቸውን አንስተው እነዚህም ከማህበረዊ ሚዲያ ንግድና ከተለያዩ ሀገራት ጥገኝነት ለመጠየቅ በሚደረግ ሙከራ ምክንያት የሚቃወሙና፣ መቃረን ብቸኛ መንገድ ነው ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች ወደ ሀገር ሲመለሱ ለውጡን የሚያደንቁ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
እውነተኛ ጥያቄ ያላቸውና በበቂ ደረጃ ምላሽ ያላገኙ ሲመስላቸው የሚቃወሙ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የእኛም ድክመት ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለውጥ ዳር በመቆም ብቻ አይሳካም መሳተፍ ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ግለሰቦች ቀረብ ብለው ይጠይቁ፣ ለውጡንም ይመልከቱ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተሳሳተ ስሌት ውጤቱን የገመቱ ሰዎች የኢትዮጵያንና የዘመኑን ነባራዊ ሁኔታ ሊገነዘቡ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ለጊዜያዊ ችግር ሲሉ ጫናን መቋቋም የሚሳናቸው ግለሰቦችም ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ስላልሆነ ለርካሽ ጥቅም ሲባል ከቁምነገር መጉደል አይሁንባችሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ታሪክ መስራት ካልተቻለ ከታሪክ ጎን መቆም እንጂ ለወቅታዊ ችግር ሲባል አቋም በማጣትና በመወላወል የሀገርን ጥቅም ማሳጣት አይገባም ብለዋል፡፡
ውጤት እና ማገናዘብ እስካለ ድረስ የሰው ልጅ እውነታው እየተገለጠለት መሄዱ እንደማይቀርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተናገሩት፡፡