የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ያሳየ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ያሳየ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ያሳየ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
6ኛው ዓመታዊ የልህቀት አመራር ጉባኤ እና የዲፕሎማሲያዊ ሲሙሌሽን (LCC 2026) የጉባኤ መክፈቻ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባኤው «አረንጓዴ አሻራ ለዘለቄታዊ የግብርና ልማት እና አረንጓዴ ኢኖቬሽን» በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
ጉባኤው በግብርና ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን፣ በሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭስ እና በሌሎች ተባባሪ ተቋማት ቅንጅት የተዘጋጀ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ፅኑ ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርናውን ማዘመንን፣ በንጹህ ኢነርጂና በፈጠራ ስራዎች ላይ ኢንቨስት ማድረጓን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
በተለይም ግብርና የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በመሆኑ በመስኖ፣ በሜካናይዜሽንና በምርታማነት ማሻሻል ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ዘላቂ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ያሳየ ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የሀገር ክብርና የደህንነት ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ወጣቶች የመፃኢዋ ኢትዮጵያ ዋና ቀራፂዎች መሆናቸውን ጠቅሰው በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ እና በበጎ ፈቃደኝነት ባህል ላይ በማተኮር ወጣቶች ላይ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ወጣቶች የሰላም እና የልማት ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ዋና የሰላም ገንቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቅንነት፣ ለሀገራቸው እና ለዓለም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።