የኢትዮጵያን ህልውና አስተማማኝ ለማድረግ በተደመረ መንገድ ወደ ብልጽግና መጓዝ ብቸኛው አማራጭ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ህልውና አስተማማኝ ለማድረግ በተደመረ መንገድ ወደ ብልጽግና መጓዝ ብቸኛው አማራጭ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ህልውና አስተማማኝ ለማድረግ በተደመረ መንገድ ወደ ብልጽግና መጓዝ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን አጽንቶ ማስቀጠል እና መገንባት ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፋፊ ውይይቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል።
ይህ ውይይት ወደ ባለድርሻ አካላት ከመምጣቱ በፊት በመንግስት ውስጥም ሰፊ ውይይቶች ይደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በእነዚህ ውይይቶችም ሀገሪቱን ለማሳደግ ባሉ አቅሞች እና ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ሰፊ ምክክር መደረጉን አውስተዋል።
እነዚህ የተደረጉት ውይይቶች የጠራ አካሄድ እና መንገድን ለመከተል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች የህዝብን የልብ ትርታ ለማዳመጥና ፍላጎቱን በግልጽ ለማወቅ ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተደረጉት ውይይቶች የኢትዮጵያውያን ፍላጎት የተቀራረበ መሆኑን ማየት አስችለዋል ነው ያሉት።
የሪፎርሙ ዋና አካል የሆኑት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስብራቶች በውይይቶቹ ውስጥ ጎልተው መታየታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ስብራቶች መጠገንም የሚያስችሉ ሀሳቦች መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ከኢኮኖሚው ወይም ከፖለቲካው አንዱን ብቻ በመክፈት ዘላቂ መፍትሄ እንደማይመጣ አመልክተው፤ ሁለቱንም ክፍት በማድረግ የምንመኛት ኢትዮጵያን መገንባት እንደምንችል እሳቤ ለመቅረጽ ውይይቶቹ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ብቸኛው መንገድ በተደመረ መንገድ ወደ ብልጽግና መጓዝ እንደሆነና የኢትዮጵያን ህልውና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ለማረጋገጥ መደመርና ማበልፀግ እንደሚገባ ወደሚያሳየው መንግስታዊ ንድፍ መገባቱን አስረድተዋል።