በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊና ማህበራዊ መጋመድ የጠበቀ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊና ማህበራዊ መጋመድ የጠበቀ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊና ማህበራዊ መጋመድ የጠበቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የታሪክ አጋጣሚዎችን በመዳሰስ የህዝቦችን የቆየ ትስስር አብራርተዋል።
ለ350 ዓመታት ገደማ የቆየውን የሸዋ ሱልጣኔት በምሳሌነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ አርጎባዎች፣ ጉራጌዎችና ሌሎች ብሔሮች በጋራ ይኖሩበት እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በህዝቦቹ መካከል የጠበቀ መጋመድ መፈጠሩን ጠቁመው በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች ዘንድ የቆየው የጉዲፈቻ ባህል ከማህበራዊ መስተጋብሩ ማሳያዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም እስከ ነገስታት ደረጃ የደረሰ የባህል መጋራት፣ አብሮ የማደግና የማህበራዊ መስተጋብር ልምምድ እንዲጎለብት ማድረጉን አስረድተዋል።
በታሪክ ሂደት በፖለቲካው መድረክ ስልጣንን ለማጠናከር ሲባል ይፈጸሙ የነበሩ ሰፋፊ ፖለቲካዊ ጋብቻዎች በህዝቦቹ መካከል እንደነበሩም ነው ያወሱት።
በሌላ በኩል፣ በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ዝውውር የተፈጠረው ሰፊ የጋብቻና የዝምድና ትስስር ህዝቦቹ ከተጋመዱባቸው መንገዶች መካከል ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በቁጥራቸው መጠንና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው ምክንያት በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የነበራቸው መስተጋብር የጎላ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ የመኖርና የመጋመድ ታሪክ እንዳላቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።