ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ለሀገር መጽናት እና ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገር ጸንቶ መቀጠል እና ለፖለቲካ አውዱ መስፋት የአማራ ክልል ህዝብ ልክ እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የአማራ ክልል ህዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ አሁን ባለውም ሆነ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሀገራዊ ለውጦች ውስጥ የፖለቲካ ስሪቱ እንዲሻሻል፣ የኢኮኖሚ ጉዞው እንዲፋጠንና አካታች እንዲሆን ትግል ማድረጉንም አውስተዋል።

ከለውጡ ማግስት በነበረው ጉዞ የአማራ ክልል ህዝብ እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት እጆቹን ዘርግቶ ለውጡን የተቀበለበትና ሀገር እንዲጸና የበኩሉን ድርሻ የተወጣበት እንደነበር ጠቁመዋል።

ከለውጡ በፊት የነበረውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መዘጋት ለመቀየር መንግስት የምህዳር ማስፋት ስራዎች ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህ የመክፈት ሂደት ውስጥ መልካም ነገሮች መታየታቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና በተከፈተው መንገድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመገዳደርና ለመጉዳት የተሰለፉ ሃይሎች እንደነበሩም አንስተዋል።

ምንም እንኳን ፈተናዎች ቢኖሩም የአማራ ክልል ህዝብ የመደመር መንገድ ብቸኛ አማራጭ መሆኑንና ለመበልጸግ የሚደረግ ጥረት ተገቢ መሆኑን ያመነ በመሆኑ፣ በዘንድሮው ምርጫ ያንን እምነቱን በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ተከባብረን፣ ጥረንና ግረን አንዲት ታሪካዊት ሀገር ማጽናት የምንችል መሆኑን ህዝቡ ያመነበት ጊዜ እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም