በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከስድስት ሺህ በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከስድስት ሺህ በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ገብተዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከስድስት ሺህ በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ ዘርፍ የተከናወኑ ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት ሽፋንን አሳድገዋል፡፡
በተለይም በገጠር አካባቢ ከግማሽ ሰዓት በላይ በእግራቸው ተጉዘው ውሃ የሚቀዱ እናቶችን እንግልት በመቀነስ በኩል ተጠቃሚነታቸውን አሻሽሏል ብለዋል፡፡
የውሃ ተደራሽነት ተረጋገጠ የሚባለው ሰዎች ከመኖሪያቸው አንድ ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት ወይም ከ30 ደቂቃ በታች የእግር ጉዞ ንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘት ሲችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው ይህም ማህበረሰቡን ወደ ዓለም ዓቀፍ የተደራሽነት ደረጃ የሚያቀርቡ ትላልቅ እርምጃዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በፌዴራል መንግሥትና ከልማት አጋሮች በሚገኝ ገንዘብ በገጠርና በከተማ አካባቢዎች የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ከስድስት ሺህ በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት መብቃታቸው ሀገራዊ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 84 ሚሊየን ወይም ወደ 75 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል፡፡
ይህም መንግሥት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትና መሠረተ ልማትን ለሁሉም ለማዳረስ የሚያደርገው ጥረት እውን መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
በተለይም ድርቅ ተጽዕኖ በሚያሳድርባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘላቂ የውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሥራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይ በተለይም በገጠር፣ ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎችና በፈጣን ዕድገት ላይ ባሉ ከተሞች ፕሮጀክቶችን በማጠናከር የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ለማሳደግ በትጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡