በአዲስ አበባ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በያዝነው ዓመትም ተጨማሪ 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን የፊታችን ሰኞ በአንድ ክንድ ተባብረው፣ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ስንታየሁ መንግስቱ፤ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ህብረተሰቡ ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በአንድነት የሚያሳትፍ ነው ብለዋል።
ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 176 የሚሆኑ ቦታዎች መለየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁን ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የችግኝና የጉድጓድ ዝግጅት፣ ችግኝ የሚተከልባቸውን ቦታዎች የመለየት፣ ተከላው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ባለሙያዎችን የማዘጋጀት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በችግኝ ጣቢያዎች የፈሉ ችግኞችን ወደ ሚተከሉባቸው አካባቢዎች የማጓጓዝ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በዕለቱ መርሀ ግብር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉና የጥላ፣ የውበትና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ በዘንድሮ የአርንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስድስት ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን ድረስ አምስት ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ኪዚህ ቀደም በችግኝ ተከላ ላይ የነበረውን ርብርብ በማሳደግ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ህብረተሰቡ የሚተክላቸውን ችግኞች በመንከባከብ በኩል ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዓመታት 90 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ሽፋኑ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡