ቀጥታ፡

አካታች በሆነው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየመከርን ነው 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፦አካታች በሆነው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየመከርን ነው ሲሉ ተመካካሪ ወጣቶች ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።

በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው ምክክር አራት ሺህ ተመካካሪዎች እየመከሩ ይገኛሉ።

በምክክር ሂደቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ያስችላል። 

ሂደቱ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ የድርሻውን የሚያበረክትበት አውድ የፈጠረ በመሆኑ፣ ለሀገር ግንባታ የሚረዱ ገንቢ ሀሳቦችን እያንሸራሸሩበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ተመካካሪ ወጣት ከበደች ኢዶሳ በሰጠችው አስተያየት፤ የምክክሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በምክክር ፈተው የተሻለች ሀገርን ለመገንባት የሚያስችላቸው ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጻለች፡፡

ምክክሩ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ያረጋገጠ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን ያሻግራል ተብሎ የሚታመንባቸው ሀሳቦች ሁሉ እየተንጸባረቁበት የሚገኝ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ምክክሩ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ትልቅ አሻራ እንደሚኖረው ጠቅሳ ሁሉም አካላት እየተሳተፉበት የሚገኝ ምክክር እንደመሆኑ ለችግሮች ትልቅ መፍትሔ መሆኑንም ጠቅሳለች፡፡

ወጣት መንግስቱ ጉሚ በበኩሉ፤ እስካሁን ያለው የምክክር ሂደት ባማረ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግሯል። 

ምክክሩ ሁሉም ሰው የሚፈልገውን ሀሳብ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያነሳበትና በነፃነት የሚወያይበት መድረክ መሆኑንም ጠቅሷል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል ብሎ እንደሚያምን ጠቅሶ ይህም የሀገሪቱን ስብራት የሚጠግን መሆኑን ጠቁሟል፡፡  

ምክክሩ ሁሉንም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያካተተና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሰው ይይ ቤምሪክ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በማጥበብና ወደ አንድነት በሚመጣ መንገድ እየተመካከሩ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም የተጀመሩ የልማት ስራዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወኑ እንደሚያስችል ተናግሯል።

ወጣት ደነቀ ዳጮ በበኩሉ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባካተተ መልኩ እየተከናወነ ነው ብሏል፡፡

ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የተፈጠረባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ተስፋ እንዳለው ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም