ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ነው -ወጣት ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ነው -ወጣት ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፦ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ተስፋ መሆኑን በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
በጉባኤው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እየተመካከሩ ይገኛሉ።
ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት ዕድሉ ከበደ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፣ የምክክር ሂደቱ ከታችኛው የውይይት እርከን ጀምሮ ደረጃውን ጠብቆ ውጤታማ በሆነ መልኩ በመግባባት መንፈስ እየተካሄደ ነው ብሏል።
ሂደቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተና በነጻነት ሀሳብ የሚንጸባረቅበት መሆኑን የገለጸው ወጣት ዕድሉ፤ በውይይቱም የጋራ ሀገርን ማስቀደም እና የሌላውን ሀሳብ ማዳመጥ ማዕከል መደረጉን ገልጿል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ወጣት ኢስራ አብዱላሂ በበኩሏ፤ የምክክር መድረኩ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተ መሆኑን አንስታለች።
ተሳታፊዎች እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመደማመጥ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መፍትሔ እንደሚያመጡ እምነቷን ተናግራለች።
ተመካካሪ ወጣት ገለታ ገቢሳ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያውያን ተደማምጠው በነጻነትና በሀሳብ ብልጫ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከራቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል።
በምክክሩ የተለያዩ ሃይማኖቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አስታውሶ፤ ምክክሩ ለሀገር ሰላምና እድገት መረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ተናግሯል።