የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን በማጠናከር ለሕዝብ አብሮነትና ዘላቂ የሀገር ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን በማጠናከር ለሕዝብ አብሮነትና ዘላቂ የሀገር ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን በማጠናከር ለሕዝብ አብሮነትና ዘላቂ የሀገር ግንባታ መሰረት የሚጥል መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተመካካሪና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባል ሙሐሙድ መሐመድ ሀሰን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
የጉባኤው ተመካካሪ ሙሐሙድ መሐመድ ሀሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አጀንዳዎች ዙሪያ ገንቢና ግልጽ ምክክር እያደረጉ ነው።
ተመካካሪዎችም የኢትዮጵያን ብዝኅነት፣ ሕብረ-ብሔራዊ እሴቶችና የጋራ ሀገራዊ ጥቅሞችን በሚያንጸባርቁ ሃሳቦች ላይ እንዲመክሩ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የሚንጸባረቁ ሃሳቦችም የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል የሚያስችል የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ በመሆኑ በተለያዩ ሃሳቦች መካከል በመተማመንና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ምክክር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን በማጠናከር ለሕዝብ አብሮነትና ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገራዊ አለመግባባቶችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ዘላቂ መፍትሔ የማያማጣና አዋጭ ያልሆነ አካሄድ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህም በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ምክክር በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ወሳኝ መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ደረጃ እያካሄደች ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ተምሳሌትና ተሞክሮ የሚሆን ውጤት እንደሚያስገኝ እምነታቸውን ገልጸዋል።