ቀጥታ፡

በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ በክረምቱ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመስጠት ተዘጋጅቷል

ባህር ዳር፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፦ በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ በክረምቱ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመስጠት መዘጋጀቱን የፓርቲው የሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ገለጹ። 

በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ "በጎነት ለእህትማማችነት እና ለሴቶች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል። 


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ፤  በክረምቱ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በክረምቱ ለአቅመ ደካሞችና የተቸገሩ ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ በደም ልገሳ፣ የትምህርት ቤት ግንባታ፣ የችግኝ ተከላ እና ሌሎችም በጎ ተግባራትን እናከናውናለን ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ  የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ዘንድሮ የ20 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚሁ መልካም ተግባር ላይ የሴቶች ክንፍ አባላት ግንባር ቀደም በመሆን እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተው ሌሎችም በተመሳሳይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝ የክልሎች የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ሃላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎችም በባህርዳር ከተማ በመዘዋወር የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም