ዓይነ ስውሩ የቧንቧ ሰራተኛ - ኢዜአ አማርኛ
ዓይነ ስውሩ የቧንቧ ሰራተኛ
ዋግ ኽምራ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፦"ዓይኖቼ ማየት ባይችሉም እጆቼ ተዓምር ይሰራሉ'' -ዓይነ ስውሩ የቧንቧ ሰራተኛ
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መለስ ጌታነህ የ62 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ አዛውንት ናቸው፤ ከጊዜ በኋላ በመጣ ችግር የሁለት ዓይኖቻቸውን ብርሃን ያጡ ቢሆንም በአካባቢው ስመ ጥር የቧንቧ ሠራተኛ ናቸው።
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው የቧንቧ ሥራ ሙያን ቀስመው፣ በዋግ ኽምራ በሚገኙ ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ለንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉ ትጉህ ባለሙያ ናቸው።
ቆላ በመውረድ፣ ደጋ በመውጣት፣ ተራራና ሸንተረሩን ሳይበግራቸው የውሃ መስመር በመዘርጋት ህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ እንዲደርሰው እያደረጉ ያሉ አዛውንት ናቸው። ለዚህም በተደጋጋሚ የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በ1991 ዓ.ም የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ ሲጀምር እሳቸው በቧንቧ ባለሙያነት በቋሚነት በመቀጠር፣ የውሃ መስመር በመዘርጋትና በመጠገን የሕክምና ክፍሎች ያልተቋረጠ ውሃ እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል።
ይሁን እንጂ ከዕለታት በአንድ ቀን ሥራቸውን እያከናወኑ ባሉበት ወቅት ባላወቁት ምክንያት የሁለት ዓይኖቻቸውን ብርሃን ያጡበት አጋጣሚ በመከሰቱ ከቤት ለመዋል መገደዳቸውን ያወሳሉ።
እንደ አቶ መለስ ገለጻ፡ “ዓይኔ ማየት ባለመቻሉ ራሴን ችዬ መንቀሳቀስ፣ እንደልቤ ሜትር ዘርግቼ ለክቼ መቁረጥና ገደል ላይ ተንጠልጥዬ የቧንቧ መስመር መዘርጋት አልችልም የሚል የተሸናፊነት ስሜት አድሮብኝ ተስፋ ቆርጬ ተቀምጬ ነበር” ይላሉ።
በዚህ ወቅት ትጋታቸውንና ብርታታቸውን የሚያውቁ የሆስፒታሉ ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ዓለማየሁ ትኩ፣ ወደ ሆስፒታሉ በመውሰድና በመምከር ሥራቸውን እንዲቀጥሉ እንዳገዟቸው አውስተዋል።
ቀስ በቀስም አቶ መለስ ሜትር በመዘርጋትና መጋዝ በመጨበጥ ልኬታን አስተካክለው፣ መገጣጠሚያ ቦታዎችን በዳበሳ ለይተው የቧንቧ ሙያ ሥራቸውን እንደገና “ሀ” ብለው ማስቀጠላቸውን አመልክተዋል።
ምንም እንኳን ከወረዳ ወረዳ ተንቀሳቅሶ መሥራት ባይችሉም፣ በግለሰብ ቤቶችና ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ የቧንቧ ጥገና ሥራቸውን በብቃት እያከናወኑ ያሉ ብቁ ባለሙያ ሆነው ቀጥለዋል።
በሆስፒታሉም ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ የውሃ መስመሮችን በመለየትና በአግባቡ በመጠገን፣ ለሐኪሞችና ለሕመምተኞች ወጥ የሆነ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ “አንቱ” የተባሉ ባለሙያ ሆነዋል።
አቶ መለስ በቧንቧ ሥራ ሳይገደቡ፣ በራዲዮ በሚቀርቡ የቴክኖሎጂ ፕሮግራሞች ባገኙት እውቀት ከአገልግሎት ውጭ የነበረውን የሆስፒታሉን የላውንድሪ (ልብስ ማጠቢያ) ማሽን በዳበሳ ጠግነው ወደ አገልግሎት በመመለስ ሆስፒታሉን ከወጪ ታድገዋል።
“ብርሃን ከዓይን ብቻ ሳይሆን ከልብና ከመዳፋችንም ይገኛል” የሚሉት አቶ መለስ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ምጣዶችን በመጠገንና ሌሎችንም የቴክኒክ ሥራዎች በመሥራት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ጠንካራ የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው።
"የዓይን ብርሃኔን አጣሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም” የሚሉት አቶ መለስ፣ አሁን ላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ጣራ ላይ በመውጣት ጭምር ቧንቧ ጠግነው የሚወርዱ ባለሙያ ሆነዋል።
“እኔ ሥራ ሳልሠራ ስውል ያመኛል” የሚሉት አቶ መለስ፣ ወጣቱ ሥራን ሳይንቅ ከሰራ ከትንሽ ነገር ተነስቶ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል ምክራቸውን ለግሰዋል።
ስለ ጉዳዩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፈራ ኃይሉ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ቢምረው እንዳሉት፡ ጋሽ መለስ የዓይን ብርሃናቸውን ቢያጡም በሙያቸው የትጋትና የ“ይቻላል” ተምሳሌት የሆኑ አዛውንት ናቸው።
አዛውንቱ በሙያቸው የሆስፒታሉ የውሃ አቅርቦት እንዳይቋረጥ በማድረግ ለሕክምና ሥራ መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸው ለሌሎች ባለሙያዎች በታታሪነት፣ በሥራ ፍቅር እና በጥንካሬ አርዓያ መሆናቸውንም ገልጸዋል።