በሰሜን ጎጃም ዞን ለመኸር ወቅት ከታቀደው ከ93 በመቶ በላይ የሚሆነው የእርሻ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎጃም ዞን ለመኸር ወቅት ከታቀደው ከ93 በመቶ በላይ የሚሆነው የእርሻ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ባህር ዳር ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፦ በሰሜን ጎጃም ዞን ለዘንድሮው የመኸር ወቅት ከታቀደው ከ93 በመቶ በላይ የሚሆነው የእርሻ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ አለኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን የሚታረሰውን መሬት በሙሉ በዘር በመሸፈን በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ለገበያ የሚሆን ምርት ለማምረት እየተሰራ ይገኛል።
ለመኸር ምርት ዘመኑ ከ332 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ እስካሁን ከ93 በመቶ በላይ የሚሆነውን መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
የተጠቀሰውን መሬት በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በሩዝ፣ በአኩሪ አተርና በቦሎቄ ሰብሎች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ መዝራት መቻሉን ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም ለዞኑ ከቀረበው ከ780 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነው እንዲሁም 38 ሺህ 700 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቀደም ብሎ የተዘራው ሰብል ቡቃያ በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ የአረም፣ የኩትኳቶና የተባይ አሰሳ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዝናብ ዘግይቶ በጣለባቸው አካባቢዎችም ያልተዘሩ ማሳዎችን ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች ለመሸፈን የዘርፉ አመራርና ባለሙያ አርሶ አደሩን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ሰሜን ሜጫ ወረዳ እንጉቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስሜነህ አበረ እንደገለጹት፤ የቀረበላቸውን ማዳበሪያ በመጠቀም በቆሎ፣ ዳጉሳና ጤፍ ዘርተዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳሁን አበበ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎና በጤፍ ዘር ሸፍነዋል።
በቂ ማዳበሪያ በወቅቱ በማግኘታቸው ዝናብ እንደጣለ ፈጥነው ለመዝራት እንዳስቻላቸው ጠቁመው፤ አሁን ላይ ቡቃያው ጥሩ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።