በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ልማት ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪ ግብዓት ለመተካት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ልማት ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪ ግብዓት ለመተካት ትኩረት ተሰጥቷል
አርባምንጭ፣ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በማዕድን ዘርፍ ልማት የግል ባለሃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪ ግብዓት ለመተካት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ማዕድን ባለስልጣን ገለጸ፡፡
መንግስት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጠባቸው አምስት ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፉ አንዱ ነው።
በማዕድን ልማቱም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርትን በራስ አቅም ለመሸፈን፣ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን ፋይዳ ለማሳደግና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለው አበርክቶ የጎላ ነው።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሔለን ዮሐንስ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ልማት የግል ባለሃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪ ግብዓት ለመተካት ትኩረት ተሰጥቷል።
በክልሉ ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የተገነባው የ"ዮ ሆልዲንግስ" የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ መንግስት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያና ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፋብሪካው ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በመተካትና በስራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ፋብሪካው የድንጋይ ከሰል በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከውጭ የሚገባውን በመተካት የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የዮ ሆልዲንግስ ፋብሪካ ጄኔራል ማናጀር ኤፍሬም ታደሰ ፋብሪካው በሰዓት 220 ቶን፣ በዓመት ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ድርጅቱ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ በማበልጸግ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ፣ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ፋብሪካው የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምርቱ በጥራቱ ከውጭ ከሚገባው ጋር የሚስተካከልና በዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን አመልክተዋል።