ለሀገራዊ ችግሮች በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት እየመከርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ችግሮች በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት እየመከርን ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሀገራዊ ችግሮች ላይ በመመካከር በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት እየተመካከሩ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ የጀመረው የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲሱ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
በጉባኤው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እየተመካከሩ ይገኛሉ።
ከተመካካሪ ምሁራን መካከል የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ኢንጂነር አልአዛር ዓባይነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በአንድ መድረክ ተሰባስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መመካከራቸው ለሀገራዊ መግባባት ግንባታ ትልቅ ዕድል ነው።
በጉባኤው በተመካካሪዎች መካከል ግልጽ፣ አሳታፊና አንዱ የሌላውን ሃሳብ በነጻነት የሚያዳምጥበትና የሚረዳበት የውይይት አካባቢ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በተመካካሪዎች መካከል ያለገደብ የሚንጸባረቁ ሃሳቦች ሀገሪቱን በተሻለ መልኩ የሚቀርጹ የጋራ መግባባቶችን ለመገንባት ወሳኝ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ የተዛቡ ትርክቶችና አለመግባባቶች ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስትፈተን መቆየቷን ያስታወሱት ኢንጂነር አልአዛር፤ የሀገሪቱን ውስብስብ ቋጠሮዎች ለመፍታት ከምክክር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው በሀገራዊ መግባባት የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለመጪው ትውልድ ብሩህ መሠረት ለመጣል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉባኤው ላይ ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ በማበርከት የታሪኩ አካል በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አባት አቶ ዘለቀ ዘውዴ በበኩላቸው፥ በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በመግባባትና በመከባበር መንፈስ ውይይት እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተመካካሪዎች የሚያንጸባርቋቸው ሃሳቦች የሀገርን አንድነትና የሕዝብን አብሮነት በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል።
በምክክር ጉባኤው ላይ እየተመከረባቸው ያሉት የሕዝብ አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና መረጋጋት ለማጠናከር ወሳኝ መሸጋገሪያ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።
የምክክር ጉባኤው በግልጽ፣ አካታችና አሳታፊ መንፈስ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ለሀገር በሚበጅ መልኩ በስኬት እየተካሄደ ነው ያሉት ደግሞ ተመካካሪ ደማይ ኮክ ናቸው።
ተመካካሪዎች በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ሰፊ ውይይቶች እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የምክክሩ አሳታፊነትና አካታችነት የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት ደማይ ኮክ፤ ከመድረኩ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ለዘላቂ ልማትና ለሰላም መስፈን መሠረት የሚሆኑ ጠቃሚ ሃሳቦች እየፈለቁ መሆኑን ገልጸዋል።