በኡማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ለዘመናት ከቆየንበት ችግርና እንግልት ታድጎናል- የአካባቢው ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኡማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ለዘመናት ከቆየንበት ችግርና እንግልት ታድጎናል- የአካባቢው ነዋሪዎች
ቦንጋ ፤ ሀምሌ 24 /2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ ዞን ኡማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ለዘመናት ከቆየንበት ችግርና እንግልት ታድጎናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ በማጠናቀቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በተለይም የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የወረዳና ቀበሌዎች ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከርና የግብይት ሰንሰለትም እንዲቀላጠፍ እየተደረገ ይገኛል።
ከሰሞኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ ዞን በአመያ ዙሪያ ወረዳ በኡማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናት ችግር ያቃለለና ለመሰረተ ልማት ጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ገዛሃኝ ገንባራ እና አቶ ገረመው ባረንጎ፤ የኦማ ወንዝ ድልድይ መገንባት የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናት ችግር የፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በክረምት ወቅት ወንዙን ተሻግሮ መሄድ አስቸጋሪ ስለነበር በተለይም ነፍሰ ጡሮች ወደ ህክምና ለመሄድ፤ አቅመ ደካሞችም ለመሻገር አይችሉም ነበር ብለዋል።
በዚህም ምክንያት በርካታ ችግሮች አልፈዋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የድልድዩ መገንባት ዘርፈ ብዙ መፍትሄዎችን ያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የባቄ ዚጋ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ አንቴቴ ዱካ፤ የወንዙ መሸጋገሪያ ድልድይ አለመኖሩ ለህክምናም ይሁን ለገበያ መሸጋገር አንችልም ነበር ብለዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ድልድይ በመግባቱ ለዘመናት የነበረብንን ችግር የፈታና ከሌሎች አካባቢዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት አስችሎናል ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ስራአስኪያጅ ኢንጂነር አብድዩ መኮንን፤ የድልድዩ መገንባት የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ከመፍታት ባለፈ በርካታ አካባቢዎችን ማስተሳሰርና ማገናኘት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በክልሉ ከኡማ ወንዝ ድልድይ ግንባታ በተጨማሪ የ177 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ መጠናቀቁን አንስተው የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቀጣይም ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ ወደ ተግባር በመግባት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅና ሌሎችንም የመገንባት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉም ተናግረዋል።