በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ ለማልማት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ ለማልማት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው
ዱራሜ ፤ ሐምሌ 24/2018ዓ.ም (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ ለማልማት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው "በተቀናጀ ግብርና የቤተሰብ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ ከቢሮው ከፍተኛ አመራሮችና ከግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት ፤በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ የማልማት ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው።
መንግስት የውስጥ አቅምን በመጠቀም ከሀገር አልፎ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲመረት እየፈጠረ ባለዉ ምቹ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በግብርናው ዘርፍ ክልሉ ያለውን የመልማት አቅም መሰረት ያደረገ ጥናት በማዘጋጀት በኢኮኖሚ ራሱን የቻለ እና ከድህነት የተላቀቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡
በመደበኛ ግብርና ስራ ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ፣ በንብ ማነብ፣ በእንሰሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ያሉ አቅሞችን ለይቶ መጠቀም በመቻሉ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ አስችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያና ለኢንዱስትሪ የሚተርፍ ምርት በማምረት የአርሶ አደሩም ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በቢሮው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ከድር መሀመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ እንደሆነም አብራርተዋል።
ከመደበኛ የግብርና ስራዉ በተጨማሪ ውስን መሬትን በመጠቀም በአረንጓዴ አሻራ ፣ በንብ ማነብ ፣ በዶሮ እርባታ ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ምርታማነት እንዲጨምር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ በማሻሻልና በምግብ ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ነው የተናገሩት፡፡