ቀጥታ፡

በምክክሩ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ነው-ተመካካሪ

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።

መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በምክክሩ ላይ ኢትዮጵያን ወደፊት ሊያራምዱ እና የታሪክ ቁስሎቻችንን ሊፈቱ የሚችሉ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።

ምክክሩ አካታችነቱን የጠበቀ መሆኑን ገልጸው፤ተመካካሪዎችም ሀሳባቸውን በነጻነት እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የሚያስማሙን ጉዳዮችን የጋራ እያደረግን መቀጠል ይገባናል ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሀገራቸው ጉዳይ እየመከሩ ነው፤ ይህም በፖለቲካ ምህዳሩ ምክክርን ባህል እያደረግን መምጣታችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዚህም የእኔ ሀሳብ ሁሌ ትክክል ነው የሚለውን እሳቤ በመተው በመመካከርና በመግባባት ሀገርን የሚያሻግሩ ሀሳቦችን እያንጸባረቅን ነው ብለዋል።

በመሆኑም የምክክር ጉባኤው ለግጭት መንስኤ የሆኑ፣ዘላቂ ሰላምን፣ልማትን የሚያደናቅፉ ችግሮችን በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም