በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች ይሸፈናል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች ይሸፈናል
አዳማ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ሸዋ ዞን የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች እንደሚሸፈን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር በርካታ ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ንቅናቄ ዋናው አካል ነው።
የዞኑ ግብርና የጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በአሁኑ ወቅት በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች በመርሃ ግብሩ ህብረተሰቡን በንቃት ለማሳተፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር ርብርብ እየተደረገ ነው።
በመርሃ ግብሩ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን ለመትከል በተሽከርካሪዎችና በሰው ኃይል የታገዘ የችግኝ ማጓጓዝ ስራ በጥንቃቄ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም በየደረጃው ግብረ ሃይል ተዋቅሮ ሂደቱን እያፋጠነ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው፤ በችግኝ ማጓጓዙ ተግባር ላይ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለማሳካትም ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ መዘጋጀቱን አቶ አብነት አስታውቀዋል።
የችግኝ ተከላው የተመረጡ ተፋሰሶችን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች የሚከናወን መሆኑን የገለጹት አቶ አብነት፣በእለቱ በዞኑ እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ለማሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በዘመቻውም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ አመራሮች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።