ቀጥታ፡

መግባባት የሰፈነባት የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ እየተመካከርን ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦አንድነትና መግባባት የሰፈነባት የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ እየተመካከርን ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መጀመሩ ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ በሆኑ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ዙሪያ በጥልቀት እየተመካከሩ ይገኛሉ።

ይህ ሀገራዊ ምክክር፣የኢትዮጵያን ችግሮች በምክክር በመፍታት ዘላቂ የሆነ ሀገራዊ መግባባት፣ሰላም እና ብልጽግናን እውን ለማድረግ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ታሪካዊ መድረክ ሆኗል።

ከተመካካሪዎች መካከል ወይዘሮ ቀለም ወርቅ መስፍን፣በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተመካካሪዎች ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ለዘመናት ለዘለቁ አለመግባባቶች መፍትሔ ለማበጀት በሰለጠነ መንገድ እየተመካከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምክክሩ አንድነትና መግባባት የሰፈነባት የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም ቀጣዩ ትውልድ በሀገራዊ ፍቅር ለሀገሩ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቅም የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።

ወጣት ደነቀ ዳሃጮ በበኩላቸው፥በኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ በሰፊው እየተመካከርን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምክክሩ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባካተተ መልኩ እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ አለመግባባቶችን በመፍታት፣ከድህነት በመውጣት ሁለንተናዊ ለውጥ እንድታመጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም መስክ አርአያ እንድትሆን ምክክሩ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ያዕቆብ ምንሾ ቀጣዩ ትውልድ ለኢትዮጵያ ጥንካሬ እና ሁለንተናዊ ብልጽግና በቁርጠኝነት እንዲተጋ አገራዊ ምክክሩ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

መድረኩ የኢትዮጵያን አዎንታዊ ገጽታና ክብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ብርሃን የሚፈነጥቅና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም