ኢዜአ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ትክክለኛ፣ ተዓማኒ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አብርሃ ግርማይ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በያዝነው ዓመትም ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን የፊታችን ሰኞ በአንድ ክንድ ተባብረው፣በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዛሬው ዕለትም የኢዜአ አመራሮችና ሠራተኞች በእንጦጦ ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አብርሃ ግርማይ እንደገለጹት፤ ኢዜአ ከአስተማማኝ የዜና ምንጭነቱ ባሻገር በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በትጋት እየተሳተፈ ይገኛል።
ተቋሙ በመረጃ ስርጭት ሀገር የመገንባት ድርሻውን እንደሚወጣ ሁሉ፣በአካባቢ ጥበቃ ላይም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋሙ ሰራተኞች በየዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ መሳተፍን ባህል እያደረጉት መምጣታቸውን ጠቁመው፥ ይህም ሀገሪቱ የያዘችውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ እና የደን ሽፋን የማሳደግ ዕቅድ በተግባር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፥የተተከሉ ችግኞች ጽድቀው ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ አስፈላጊው የእንክብካቤና የጥበቃ ስራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ በተከናወነው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ የተሳተፉት የኢዜአ አመራሮችና ሰራተኞች አረንጓዴ፣ውብና ምቹ ኢትዮጵያን መገንባት የትውልዱ አደራ ነው ብለዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡት በተቋሙ የህግ፣ ስነ-ምግባርና ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ፤ ተቋሙ የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን በተግባር እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተከላ በኋላ ችግኞቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲበቁ የተለመደውን የዘወትር እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ ለስድስተኛ ጊዜ መሳተፋቸውን የገለጹት የተቋሙ የንብረት አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ ብዙአየሁ አባተ፤የተከሏቸው ችግኞች እንዲጸድቁ አስፈላጊውን ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና ለምነቱን ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰው ሃብት አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ ሀገሬ ተስፋሁን ናቸው፡፡
ችግኞች እንዲፀድቁ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኢዜአ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለሀገሪቱ የደን ሽፋን እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡