ቀጥታ፡

ለሁላችንም የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በምክክር ችግሮችን የምንፈታበት ጊዜ አሁን ነው

ገንዳውኃ፣ ሐምሌ 24/2018(ኢዜአ)፡- ለሁላችንም የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በምክክር ችግሮችን መፍታት አለብን ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በምክክር ኢትዮጵያን ከግጭትና ጦርነት አዙሪት በማውጣት ዘላቂ ሰላምና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሀገራዊ የምክክር ሂደት ወሳኝ መፍትሄ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል። 

በዚህም መሰረት የህዝብን አጀንዳ በመሰብሰብና በማደራጀት ካጫፍ ጫፍ የተወከሉ ወገኖች በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።

የምክክሩ ሂደት ከዝግጅት ጀምሮ አጀንዳ በማሰባሰብና በመለየት የተሄደበት መንገድ የሂደቱን ስኬታማነት የሚያመላክት ሲሆን ታሪካዊው የምክክር ሂደት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

የምክክር ሂደቱን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በምእራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች፤  ችግሮችን ለመፍታትከምክክር የተሻለ አማራጭ የሌለ በመሆኑ እድሉን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ሹመት ምስጋናው፤ አቶ ጀማል አብዱልቃድር እና አቶ የማታው ታረቀኝ፤ ለሁላችንም የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ከምንም በላይ ችግሮችን በምክክር መፍታት ጥላቻን በፍቅርና ይቅርታ መተካት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በምክክር ችግሮችን የምንፈታበት ጊዜው አሁን ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌዎቹ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገራችን ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ምክክር ላይ መገኘታችን ታሪካዊ እድል በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። 

በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን የምክክር እድል ወደ ጎን በማለት አሁንም ለግጭትና ጦርነት የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን አንስተው ከዚህ መጥፎ ተግባር በመውጣት ለሰላም ግንባታ የሚሰራበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና አንዱ ለሌላው ጋሻ የመሆን ታላቅ እሴት እንዳለው አንስተው ይህንን መልካም እሴት ማጠናከርና ለሁሉም የምትመች ጠንካራ ሀገር መገንባት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በምክክር ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት፤ ጠንካራ ሀገር ለመገንባትና ለልጆቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ለመስራት በጋራ እንቁም በማለት የሀገር ሽማግሌዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም