የጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች እድሳት ለከተማዋ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው-ጎብኝዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች እድሳት ለከተማዋ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው-ጎብኝዎች
ጎንደር፤ሐምሌ 24/2018(ኢዜአ)፦የጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች እድሳት ለከተማዋ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ጎብኝዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አመራሮች፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች የጎንደር ከተማን ታሪካዊ ቅርሶች ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የፋይናንስ ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ ጥሩየ ገሰሰ እንደገለጹት፥ የተካሄደው የቅርሶች ጥገናና እድሳት ታሪካዊ እሴቶች የቀድሞ ይዘታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቅርስ እድሳቱና የኮሪደር ልማቱ ለቱሪስቶች፣ባለሀብቶችና ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን የፈጠረ በመሆኑ ሌሎች እንግዶችም ወደ ጎንደር መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ ትውልድ ስለ ሀገሩ ታሪክና ቅርስ በአግባቡ በመረዳትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር ዘርግቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት።
ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሰፊ የማስተዋወቅ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የመጡት አቶ እሸቱ ገላጋይ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ቅርሶቹ የመፍረስ አደጋ ተደቅኖባቸው እንደተመለከቱ ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የፋሲል አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች ታድሰውና በኮሪደር ልማት ተውበው በመመልከታቸው ታላቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም በበኩላቸው፤ ከ15 ዓመታት በፊት ጎንደርን ሲጎበኙ የነበረው የእርጅና ገጽታ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ መቀየሩን ነው የሚናገሩት።
ከአብያተ መንግሥታቱ በተጨማሪ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታም በጥሩ ሁኔታ እየታደሰ መሆኑን መመልከታቸውንም ነው የተናገሩት።
ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በተመቻቸና በተዋበ ቦታ ሆነው በዓሉን እንዲታደሙ የሚያስችላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ግምገማ መድረክ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።