ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ የግብርና ምርታማነትን ጨምሯል

ዲላ፣ ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ) ፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የግብርና ምርታማነትእንዲጨምር ማስቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን ሰኞ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ ለመሥራት እንዘጋጅ በማለት ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

"በእነዚህ ቀናት ውድ የሀገሬ ልጆች አስፈላጊውን ዝግጅት እንድታደርጉና በጋራ ተስፋን እንትከል" በማለትም መልዕክት ማስተላለፋቸውም እንዲሁ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ትግበራ የግብርና ምርታማነት መጨመሩን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ከ16 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ተከላው ልየታ በተከናወነላቸው 1 ሺህ 345 ስፍራዎች እና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

ለዚህም የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የችግኝ አቅርቦትና የሰው ኃይል ስምሪት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

የአንድ ጀምበር ተከላው በላቀ የሕዝብ ተሳትፎ የሚፈጸም መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ ከ2 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሳተፉም አብራርተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገርን የማውረስ ጥረት አካል መሆኑን በመጠቆም፣ ሕብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም