ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር ለሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ልማት መረጋገጥ ያግዛል-ምሁራን

መቱ፤ሐምሌ 24/2018 (ኢዜአ):-ሀገራዊ ምክክሩ በሀሳብ ልዩነቶች ላይ ድልድይ በመገንባት ለኢትዮጵያ ሰላም፣ጸጥታና ዘላቂ ልማት መንገድ ያበጃል ሲሉ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።


የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀገሪቷ ከቆየችበት የኃይልና የግጭት አዙሪት ወጥታ ወደ ሰላማዊ የመደማመጥ፣ የመወያየትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደ ድልድይ ያገለግላል።

በልዩነቶች ውስጥ አንድነትን በመፍጠር ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተቀመጠ ታሪካዊና መዋቅራዊ መሠረት ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው ሀገራዊ ምክክር የሀሳብ ልዩነትን በማጥበብ ለሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ልማት መረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።

ከምሁራኑ መካከል የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በድሉ ተካ(ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ የተለያየ የማሕበረሰብ እሴቶች ዙሪያ በቂ የሆነ እውቀትና ምልከታ ያላቸው ተሳታፊዎችን ያካተተ በመሆኑ ጥሩ ውጤት ይገኝበታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

አንድ ሀገር በቂ ሀብት እንዲሁም ጥሩ የሚባል ፖለቲካ ማራመድ መቻሏ ብቻውን ለሰላምና ልማት መረጋገጥ ዋስትና አይሆንም ያሉት ዶክተር በድሉ፤ሁሉም በሀገርና ሀገራዊ ጥቅም ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም መኖሩ ወሳኝና መሠረታዊው ጉዳይ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ብዝኃነት የሚስተናገድባት ሀገር በመሆኗ፣እነዚህን ልዩነቶች ከሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና ከሀገራዊ ጥቅም አንጻር በጥንቃቄ መቃኘት እንደሚገባም አስምረውበታል።

ከሰላምና ጸጥታ፣ከፖለቲካ እንዲሁም ከልማትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሀገራዊ ልዩነቶችና ችግሮች የሚጠበቁ ቢሆኑም፣በአግባቡ ካልተያዙ ለበለጠ ውስብስብ ችግሮች ምንጭ ሲሆኑ ማየት የተለመደ መሆኑንም አንስተዋል።

እናም እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ለተለያዩ ሀገራዊ ችግሮች አጋላጭ የሆኑትን የሀሳብ ልዩነቶች በማጥበብ ለሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ትልቅ መሠረት የሚጥል ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

በዩኒቨርሲቲው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና መምህር ዘነበ ረታ ሮባ በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ምክክሩ ብዙሃንን ያሳተፈ መሆኑን ተከትሎ የሀሳብ ልዩነቶችን በማጥበብ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ የሚያመጣ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ለልማት ጠንቅ የሚሆኑ የሐሳብ ልዩነቶች በመፍታት ለልማትና እድገት ወሳኝ እና ዋና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ለሀገር የሚበጁ መሰረቶች የሚጣሉበት መሆኑን አንስተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላምና ጸጥታ፣የልማት ተጠቃሚነትና ሌሎች ጉዳዮችን መነሻ አድርገው እየተፈጠሩ ለሚገኙ ችግሮችና ልዩነቶች የጋራ ሀገራዊ መፍትሔን የሚያመጣ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህሯ አልማዝ ተሾመ ናቸው።

ለሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ ያልሰጡ የሐሳብ ልዩነቶች ለሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሚሆኑ በማንሳት፤የሰላም መደፍረስ ደግሞ እንደሀገር የታቀዱ የልማትና እድገት ግቦች እንዳይሳኩ እንቅፋት እንደሚሆን መምህር አልማዝ ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የሐሳብ ልዩነቶች ለሀገር ሰላም፣ ልማትና እድገት መሆን በሚችሉባቸው አውድ ተቃኝተው ለተያዙ የልማትና እድገት ግቦች መረጋገጥ በጋራ መስራት ለሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም