ቀጥታ፡

የተጀመረው የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ በቴክኖሎጂ፣ በፍጥነት፣ በፈጠራ፣ በጥራትና በታማኝነት ማስፋፋቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)የተጀመረው የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ በቴክኖሎጂ፣ በፍጥነት፣ በፈጠራ፣ በጥራትና በታማኝነት ማስፋፋቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገነዘቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ሀገር በቀል ሆኖ በሰባት አምዶች ተደራጅቶ የተቀረጸውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር አፈጻጸም ሪፖርት ለሪፎርም ምክር ቤቱ ቀርቦ በዝርዝር ተገምግሟል ብለዋል።

አምዶቹም ዘመኑን የዋጀና በተዋረድ የተናበበ አደረጃጀት፣ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ስምሪት፣ ብዝሃነት፣ ዲጂታላይዜሽ፣ የለውጥ አመራር እና የአገልግሎት ማሻሻያን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አፈጻጸሙም ፍጥነትን፣ ፈጠራን፣ ፈጻሚዎቹን ባለቤት ማድረግንና ዘላቂ ሥርዓት ግንባታን መሠረት ተደርጎ በጥብቅ ዲስፕሊንና በእውቀት ውጤታማ እና ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑንም አይተናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

በሪፖርቱ ሰው ተኮር በሆነ ሁኔታ የመሶብ አገልግሎትን በማስፋፋት ሂደት ጉልህ የሚባል መሻሻል በየከተሞቹ ታይቷል ሲሉም አስታውቀዋል።

በመልዕክታቸው አክለውም በአገልግሎት ማሻሻያ ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የምንችል መሆኑንና በዜጎች በኩል የነበረውን እሮሮ መፍታት መጀመራችን በተግባር የታየበትም ጉዳይ ነው ብለዋል።

የተጀመረው የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ በቴክኖሎጂ፣ በፍጥነት፣ በፈጠራ፣ በጥራትና በታማኝነት ማስፋፋቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋለ

ለዚህም ሥራ የጠራ መረጃ ማደራጀት፣ ቴክኖሎጂን ማበልጸግና የሰራተኞችን ብቃት ማጠናከር የቀጣይ ትኩረት እንዲሆን በምክር ቤቱ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም