ቀጥታ፡

ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ታጠናክራለች - የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ በማላቅ አጠናክራ እንደምትቀጥል የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኦሊቪዬ ዣን ፓትሪክ ንዱሁንግሬሄ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በተመሳሳይ የፓን-አፍሪካኒዝም እሴቶች የተሳሰሩ ለአፍሪካ አንድነትና ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የቆዩ ወዳጅ ሀገራት ናቸው።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ ጥቅምና በመተማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ በንግድ፣ በጤና፣ በመከላከያ፣ በትምህርት እና በሌሎች ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያለውን ትብብር የበለጠ ለማስፋት ሁለቱም ሀገራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።

አሁን በኢትዮጵያ 130 የሩዋንዳ ተማሪዎች በህክምና ዘርፍ በማስተርስና በዶክትሬት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል የጤናና የከፍተኛ ትምህርት ትብብር እየጠናከረ መምጣቱን የሚያሳይ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመከላከያ ዘርፍም የሩዋንዳ መከላከያ ሠራዊትና የብሔራዊ ፖሊስ አባላት በኢትዮጵያ የሙያ ሥልጠና እየተከታተሉ መሆናቸው የሁለቱን ሀገራት የጸጥታና የመከላከያ ትብብር ይበልጥ እያጠናከረ መምጣቱን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ለአፍሪካ አንድነትና ለአህጉራዊ ውህደት በተለያዩ መድረኮች ጉልህ ሚና ሲጫወቱ የቆዩ ሀገራት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታና በአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት መገንባት ውስጥ የተጫወተችው ታሪካዊ ሚና፤ ሩዋንዳ በ2018 ያስተናገደችው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የተፈረመበት ታሪካዊ ጉባኤ የሁለቱን ሀገራት የፓን-አፍሪካኒዝም አመራር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት፣ አህጉር አቀፍ ንግድንና የጋራ ልማትን ለማፋጠን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

አፍሪካ በወጣት የሰው ኃይል፣ በተፈጥሮ ሀብትና በለም መሬት ብልጽግና ብትታወቅም፣ በፋይናንስና በአመለካከት ተግዳሮቶች ምክንያት ያላትን ሙሉ አቅም አለመጠቀሟን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሕብረትን ተቋማዊና የፋይናንስ ማሻሻያዎች በማፋጠን የአህጉሪቱን የልማት ፕሮጀክቶች በራሷ ሀብት ለመደገፍ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ አመራር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን እየጎዳ በመሆኑ ሀገራቱ በዚህ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ ይገባቸዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት፣ በደን ልማትና በአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም መርሃ ግብሮች ያካበተችውን ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ በመሆን በደቡብ–ለደቡብ ትብብር ማዕቀፍ መጋራት የአካባቢ ጥበቃንና የአህጉሪቱን ዘላቂ ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በጋራ እሴቶች፣ በፓን-አፍሪካኒዝም መርሆችና በጋራ ልማት ራዕይ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር በማስፋት ለአፍሪካ አንድነት፣ ለአህጉራዊ ኢኮኖሚ ውህደትና ለዘላቂ ልማት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኞች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም