በተቃርኖ የተሞላው ሕገ ወጡ ሕወሓት የጥፋት ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
በተቃርኖ የተሞላው ሕገ ወጡ ሕወሓት የጥፋት ጉዞ
የሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የፖለቲካ ጉዞ በበርካታ መሠረታዊ ተቃርኖዎችና የፖለቲካ ስህተቶች የተሞላ ነው። ቡድኑ በትግል ጊዜም ይሁን ሀገርን በመምራት ባደረገው የፖለቲካ ተሳትፎ ታሪክ ይቅር የማይላቸው ስህተቶችን ፈጽሟል። ከሁሉም በላይ የትግራይን ሕዝብ ለዘመን ተሻጋሪ መከራና ስቃይ ዳርጓል። የወጣቶችን ተስፋ እና ሕልም አጨልሟል። የሕገ ወጡ ቡድን በተቃርኖ የተሞላ ጉዞ በጨረፍታ እንመልከት።
ተቃርኖ አንድ፦ የሀገር ገዥነት እና የነጻ አውጪነት መንፈስ
ሕገ ወጡ ሕወሓት ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ ሀገር በመራበት ዘመንም ጉዞው በተቃርኖ የተሞላ ነበር። በዚህ የሥልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፤ ከኅብረት ይልቅ መነጠልን ሥር እንዲሰድ አድርጓል። በስም ደረጃ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት እንደሚያራምድ ቢናገርም ለኢትዮጵያውያን የተለያየ የዳቦ ስም በመስጠት እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ በማድረግ የጥላቻ ፖለቲካን አንግሷል።
የሕግ የበላይነት እና የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በአንዱ ቡድን ላይ የማይተገበር ሌላው ላይ ግን ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል። ከቡድኑ ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸው ቡድኖች ለሕግ የማይገዙ፣ ከኮንትሮባንድ እስከ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ውስጥ የሚሳተፉ ነበሩ። ሌላው ጽንፈኛ፣ አክራሪ እና ተስፋፊ ተደርጎ በሽብር እየተወነጀለ በየማረሚያ ቤቱ እንዲንገላታ ተደርጓል። በጥቅሉ ሕገ-መንግሥት እና የፌዴራል ሥርዓትን ለራሱ በሚያመች መልኩ ሲጠቀምበት ቆይቷል።
ከዚህም ባለፈ ሕገ ወጡ ቡድን ሀገርን እየመራ እንደ አንድ የክልል ነጻ አውጪ ድርጅት በብሔሮች መካከል ጥርጣሬና ልዩነት እንዲሰፋ የሚያደርጉ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካዎችንም አንግሷል። ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ፖለቲካን ከማካሄድ ባለፈ ‘ልዩ ኃይል’ በሚል ወታደራዊ አደረጃጀት ፈጥሮ መንግሥት መስሎ ሀገርን የማፍረስ እና የማዳከም ተግባር ውስጥ ተሳትፏል።
ተቃርኖ ሁለት፦ ሰሜን እዝን ባጠቃበት ጊዜ
ሕገ ወጡ ቡድን ራሱ ያደራጀውን እና ሲያሞካሸው የቆየውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥቅምት 2013 ዓ.ም. በማጥቃት የተቃርኖ ጉዞውን መቀጠሉን አረጋግጧል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ የትግራይ ሕዝብ ጋሻና መከታ፣ የችግር ጊዜ ደራሽ እና ከሻዕቢያ ተከላካይ ሆኖ ላቡንና ደሙን ገብሯል። ሕገ ወጡ ቡድን የሀገር ሉዓላዊነትና የሕገ-መንግሥት ጠባቂ ነኝ ሲል ቆይቶ፣ ለ20 ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ላይ የነበረውን እና የትግራይ ተወላጆችንም በሠራዊቱ ውስጥ ያቀፈውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አጥቅቷል።
ሴረኛው እና በተቃርኖ የተሞላው ቡድን የማይመርዝና የማይለውጠው መሆኑን ያረጋገጠበትን ድርጊት ፈጽሞ የሀገር ጋሻና መከታን አዋርዷል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳፋሪ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። የተቃርኖው ውጤት ግን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልተጠበቀ ሁኔታ አንድ ላይ አስተሳሰረ፤ ለሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የአባቶቹን ታሪክ እንዲደግም ዕድል ፈጠረ።
ተቃርኖ ሦስት፦ የሰላም ውል እና የውስጥ ክፍፍል
ሕገ ወጡ ቡድን የሥልጣን ጥመኝነቱን ለማርካት ስፍር ቁጥር የሌላቸው የትግራይ ክልል ተስፋ የሆኑ ወጣቶችን በጦርነት ከማገደ በኋላ የሰላም ስምምነት ተፈረመ። በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ጦርነቱን ለማስቆም የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ነበረ። ነገር ግን ከስምምነቱ በኋላ አሁንም ከስህተቱ የማይማረው ይህ ቡድን የተቃርኖ ጉዞውን መቀጠሉን ያረጋገጠበት ጥፋት ፈጸመ።
ሕገ ወጡ ቡድን ስምምነቱን በይፋ ከተቀበለው በኋላ ስምምነቱን የሚጥሱ ድርጊቶችን መፈጸም ቀጠለ። መሣሪያ ለማስረከብ ተስማምቶ በስምምነቱ መሠረት መሄድ አቃተው፣ እንቅፋት ፈጠረ። በትጥቅ ውስጥ የቆዩ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ ነበረበት፣ አላደረገም። ይልቅስ ለሌላ ጥፋት ውስጥ ለውስጥ መዘጋጀቱን ተያያዘው።
ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመስረት ተስማምቶ ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችን አልቀበልም በማለት ሕገ ወጥነቱን ቀጥሎ ለትግራይ ሕዝብ ሰላም እና እፎይታ የሰጠውን የሰላም ስምምነት አፈረሰ። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ትኩረት መደረግ የነበረበት የወደሙ አካባቢዎችን መገንባት፣ የተፈናቀሉትን መመለስ እና ሰብዓዊ እርዳታ ማፋጠን ላይ መሆን ሲገባው፣ ሕገ ወጡ ቡድን ወደ ውጭ ይፋ በወጣ የሥልጣን ሽኩቻና የእርስ በእርስ ውንጀላ ውስጥ መዘፈቁ ለሕዝቡ ያለው ግድየለሽነት ማሳያ ሆኖ ተወሰደ።
ለጥፋት ተልዕኮው ስኬት በፍጹም የዓላማም ይሁን የትግል አንድነት የለኝም ሲላቸው ከነበሩ የጥፋት ቡድኖች ጋር አበረ። ይህ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመመሳጠር ሉዓላዊነትን ለማስደፈር እና ሀገር ለማፍረስ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ጀመረ። ልብ ማለት የሚገባን ባህር በርን የሚያክል ጉዳይ እንደ ተራ ሸቀጥ ያየው ቡድን እንዴት ስለ ብሔራዊ ክብር እና ሉዓላዊነት ሊያስብ ይችላል? ሊሆን አይችልም።
ተቃርኖ አራት፦ የሕገ ወጡ ቡድን የመጨረሻው የጥፋት ጉዞ
ዓለምና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀየርም፣ ሕገ ወጡ ሕወሓት ግን አሁንም በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የትግል ስልት ተከተሏል።
ቡድኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከሆኑት ባዕዳን ተልዕኮ ተቀብሎ ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር አብሯል። ‘ጽምዶ’ ከተባለው የጥፋት ስብስብ ፊት አውራሪ በመሆን የለመደውን የተቃርኖ ጉዞ ለመቀጠል ተቅበዝብዟል። የወጣቱን የሥራ፣ የዲሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና የዘመናዊነት ጥያቄ በትክክለኛ መንገድ ከመመለስ ይልቅ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ለሚያደርገው የቀቢጸ ተስፋ ሙከራ እያደረገ ነው። ከምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ሕጋዊ ሰውነት የማጣት አለመግባባት እና በሕጋዊ መንገድ ራሱን ለማደስ ፈቃደኛ አለመሆኑ ቡድኑን በሕግ ፊትም ሆነ በፖለቲካዊ ምህዳሩ ውስጥ ወደ መጨረሻው የመገለልና የውድቀት ምዕራፍ መርቶታል።
ዛሬ ግን ትናንት አይደለም። ኢትዮጵያ ዘመኑን በዋጀ አመራር እየተመራች ትገኛለች። ዘመኑን ሙሉ የተቃርኖ ጉዞ ያደረገው ሕገ ወጡ ቡድን ወደ መጨረሻው የፖለቲካ ውድቀት እያመራ ነው። የሕገ ወጡ ቡድን የተቃርኖ ጉዞም የበቃል።