በምዕራብ ሸዋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል
አምቦ ፤ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ):- በምዕራብ ሸዋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
በዞኑ አደአ በርጋ ወረዳ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በምረቃ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በዞኑ በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በ2018 በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የተገነቡ 585 ፕሮጀክቶች ተጠናቀቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
"የማንጨርሰውን ፕሮጀክት አንጀምርም" ብለን ለህዝባችን ቃል በገባነው መሰረት ሁሉንም ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በማብቃታችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል በማለትም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የአደኣ በርጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ በቀለ በበኩላቸው፤ በወረዳው በመንግሥት በጀትና በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከ 274 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 33 የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ዛሬ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል፣ የቅድመ መደበኛና አንጀኛ ደረጃ "ኦልማ አዳ" ትምህርት በቶች፣ ሞዴል የህዝብ መድሃኒት ቤት፣ የከብቶች ማድለቢያና ለዶሮ እርባታ የሚሆኑ ሼዶች እና የኢንጭኒ ከተማ ኮሪደር ልማት ይገኙበታል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ከመመለስና የመልካም አስተዳደር ችግርን ከመፍታት ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩላቸውም ገልጸዋል።
በወረዳው ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሰላም እጦት ችግር እንደነበረና አሁን ላይ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በተገኘው ሰላም የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ጠቁመዋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታ የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው መልስ ያገኘበት በመሆኑ መደሰታቸውን በመግለጽ፤ አሁን ያገኙትን ሰላም በማፅናት የተመረቁ ፕሮጀክቶችን እየተንከባከቡ ለመጪው ትውልድ እደሚያሳልፉ ተናግረዋል።
ከአከባቢው ነዋሪዎች መካከል አባ ገዳ ግርማ ዱጉማ፤ ፕሮጀክቶቹ የረጂም ጊዜ ጥያቄያቸው የተመለሰበት ስለሆነ ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ተዋበች በቀለ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የተሰራው ሞዴል የህዝብ መድሃኒት ቤት የነበረባቸውን የጤና አገልግሎት ችግር ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ ደስታቸውን ገልጸዋል።