ቀጥታ፡

ከሀገር አቀፍ ንቅናቄ እስከ ዓለም አቀፍ እውቅና፦የአረንጓዴ አሻራ ውጤታማ አበርክቶ

በታዋቂ ዓለም አቀፍ የሳይንስ መጽሔቶች ላይ የታተሙ ተከታታይ ጥናቶች  የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በደን መልሶ ማልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተዕፅኖን በመከላከል ፣ የካርበን ክምችት በማሳደግ እና በማህበረሰብ ተሳትፎ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ መሆኑን አረጋገጡ።

የጥናቱ ግኝቶች ከስምንት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)አነሳሽነት የተጀመረው የአረጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ በአፍሪካ ግዙፍ እና እጅግ ውጤታማ ወደሆነ የመሬት ገጽታ መልሶ ማልማት ፕሮግራም ማደጉን የሚያሳይ ጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ አቅርበዋል።

ኔቸር ፖርትፎሊዮ (Nature Portfolio)፣ ኤልሴቪየር (Elsevier) እና ስፕሪንገር (Springer)ን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው አሳታሚዎች እ.ኤ.አ. በ2026 የወጡ አምስት ጥናቶች፤ የሳተላይት ምስሎችን፣ የመስክ የዳሰሳ ጥናቶችን፣ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂዎችን እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የመርሐ-ግብሩን አካባቢያዊ ፋይዳ ገምግመዋል።

ከፍተኛ የችግኝ ጽድቀት ምጣኔ - የውጤታማ መልሶ ማልማት ማሳያ

በኤልሴቪየር 'ትሪስ፣ ፎረስስ ኤንድ ፒፕል' (Trees, Forests and People) መጽሔት ላይ የታተመ ጥናት (አሰፋ እና ሌሎች፣ 2026) እንዳመለከተው፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተተከሉ የዛፍ ችግኞች 80 በመቶ የሚገመት የጽድቀት ምጣኔ አስመዝግበዋል፤ ይህም ከሌሎች በርካታ ሰፊ የደን ልማት ፕሮግራሞች ልቆ የተገኘ ነው።

ተመራማሪዎቹ ለዚህ ስኬት በዋነኛነት የጠቀሷቸው የተሻሻሉ የመልሶ ማልማት ልምዶችን ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል በዋናው የክረምት ወቅት መትከል፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የቦታ ምርጫ፣ እንዲሁም በቴክኒክ ስልጠና የታገዘ ጠንካራ ማህበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ ይገኙበታል።

የጥናቱ መሪ ዶ/ር ታደሰ አሰፋ እንደገለጹት፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንሳዊ የደን አያያዝ ጋር ማቀናጀት አዳዲስ ተከላ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ የችግኝ መትከያ ቦታዎች ብቻ ሆነው ከመቅረት ይልቅ ዘላቂ ወደሆነ ደንነት እንዲያድጉ አስችሏል።
 

የማህበረሰብ ተሳትፎ ለስኬቱ ሞተር ነው

በስፕሪንገር 'ዲስከቨር ኢንቫይሮመንት' (Discover Environment) ላይ የታተመ ሌላ ጥናት ደግሞ ሰፊው የማህበረሰብ ተሳትፎ የመርሐ-ግብሩ ታላቅ ጥንካሬ መሆኑን አመልክቷል።

የጥናቱ መሪ ዶ/ር አብዱረዛቅ ሀጂ እንዳስገነዘቡት፣ እያደገ የመጣው የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እና በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የህዝብ ተነሳሽነት፣ አባወራዎች ችግኝ መትከልን የአካባቢን የመቋቋም አቅም ለመገንባት፣ ለዘላቂ ግብርና እና ለወደፊት የኑሮ መሰረት እንደተደረገ ኢንቨስትመንት እንዲመለከቱት አድርጓል።

የህዝብ ተሳትፎ የመርሐ-ግብሩ የረጅም ጊዜ ስኬት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ጥናቱ በማጠቃለያው አስቀምጧል።

የደን ሽፋን ማደግ የአካባቢን አየር ንብረት ያሻሽላል

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቡኖ በደሌ ዞን የተካሄደ ጥናት በስድስት ዓመታት ውስጥ የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን፣ ማለትምከ27.64 በመቶ ወደ 38.24 በመቶ ከፍ ማለቱን አስመዝግቧል።

ጥናቱ የመሬት ገጽ የሙቀት መጠን እስከ 1.16 ዲግሪ ሴልሺየስ መቀነሱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ይህም የደን ሽፋን መስፋፋትየአካባቢውን አየር ንብረት እያሻሻለ እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን እያጠናከረ መሆኑንያሳያል።

እነዚህ ለውጦች የስነ-ምህዳር አገልግሎቶችን እንደሚያሳድጉ እና የግብርና ምርታማነትን እንደሚደግፉ ይጠበቃል ሲሉ ተመራማሪዎቹተናግረዋል።

ጥናቶች ከፍተኛ የካርበን ክምችት አቅም መኖሩን አጉልተዋልበኔቸር ፖርትፎሊዮ (Nature Portfolio) ሥር በ'ሳይንቲፊክ ሪፖርትስ' መጽሔት ላይየወጣ ሌላ ጥናት፣ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች እና የግብርና-ደን ሥርዓቶች ከፍተኛ መጠንያለው የካርበን ዳይኦክሳይድ ክምችት የመያዝ አቅም እንዳላቸው አረጋግጧል።

አንዳንድ መልመው ያገገሙ መሬቶች በሄክታር ወደ 500 ሜጋግራም የሚጠጋ የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን የያዙ መሆናቸው የተረጋገጠሲሆን፣ ይህም መርሐ-ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን በማቃለል ረገድ ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያሳያል።

የደን መልሶ ማልማት ስራውን ማስፋፋት የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃ ተሳትፎ የበለጠ እንደሚያጠናክርናበማደግ ላይ ባለው የዓለም አቀፍ የካርበን ገበያ ላይ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
 

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የደን ዕድገቱ እንደሚቀጥል ተንብዮአል

ማሽን ለርኒንግ፣ የሳተላይት ምስሎች እና የጂኦስፓሻል ትንታኔዎችን በመጠቀም በስፕሪንገር 'ኢንቫይሮመንታል ሞኒተሪንግ ኤንድአሴስመንት' (Environmental Monitoring and Assessment) መጽሔት ላይ የታተመ ሌላ ጥናት እንዳመላከተው፣አሁን ያለው የመልሶ ማልማት ጥረት ከተቀጠለ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ቢያንስ እስከ 2035 ድረስ መስፋፋቱን እንደሚቀጥልተንብዮአል።

በመሬት ገጽታ መልሶ ማልማት ላይ የሚደረገው ተከታታይ ኢንቨስትመንት የደን ሽፋንን የበለጠ እንደሚያሳድግ፣ የካርበን ክምችትንእንደሚያጠናክር እንዲሁም የኢትዮጵያን የአየር ንብረት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን እንደሚደግፍ ጥናቱ ያሳያል።
 

ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ እውቅና

በአጠቃላይ ሲታይ፣ አምስቱ ገለልተኛ ጥናቶች የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሁለንተናዊ ሳይንሳዊ ግምገማ በማቅረብ፤በደን መልሶ ማልማት፣ በካርበን ክምችት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እና በህዝብ ተሳትፎ ረገድ የሚለኩና ተጨባጭ ውጤቶችንማምጣቱን ደምድመዋል።

እነዚህ ግኝቶች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የሰፊ ሥነ-ምህዳር መልሶ ማልማት ቀዳሚ ሞዴል በማድረግ ያስቀመጡትሲሆን፤ ዘላቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ሳይንሳዊ ዕቅድ እና አገር አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ እንዴት ተጨባጭ የአካባቢ ጥበቃ ውጤቶችንማምጣት እንደሚችሉና፣ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመሬት መራቆትን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖእንደሚያበረክቱ በጉልህ አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም