በጅማ ዞን የተገነቡ ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን የተገነቡ ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርገዋል
ጅማ፤ ሀምሌ 23/2018 (ኢዜአ) ፡-በጅማ ዞን በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ማድረጋቸውን የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር ገለጹ።
በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የግብርና ግብዓት ማከማቻ፣ የመንገድ፣ ድልድይ ፣የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኬላ፣ የገበያ ማዕከል እና የወረዳው አስተዳደር ህንፃን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር በወቅቱ እንዳሉት የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው ።
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት እና በህዝብ ተሳትፎ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርገዋል ብለዋል ።
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት በ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ከ1 ሺህ 876 በላይ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል ።
ፕሮጀክቶቹ ለህዝብ ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልከሪም አባራያ በበኩላቸው በወረዳው በበጀት ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸው ከተጀመሩ 33 ፕሮጀክቶች ውስጥ 23ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ብለዋል።
ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረጉ አመላክተዋል ።
የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተደረገ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሀመድ ዘይን ተማም ናቸው።
አቶ አበዱላሂ አባ ጀበል በበኩላቸው በወረዳው ዶዩ ቃጨማ ቀበሌ የተገነባው የግብዓት ማቆያ እና ማከማቻ ከዚህ ቀደም የግብርና ግብአቶችን ለማግኘት ወደ አጎራባች ወረዳዎች በመጓዝ የሚባክንን ግዜና ገንዘብ እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።