ቀጥታ፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር 70 ሚሊየን ደርሷል

ጎንደር፤ሀምሌ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በመላው ሀገሪቱ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር 70 ሚሊየን መድረሱን የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት "የተሻለ የጤና መድህን አገልግሎት ለህዝባችን ጤናና ደህንነት" በሚል መሪ ቃል ያለፈውን በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የአዲሱን በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ እያካሔደ ይገኛል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የጤና መድህን አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ በማድረግ ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለመገንባት ወደ ስራ ተገብቷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአባላቱን ቁጥር 70 ሚሊየን በማድረስ፤ ከ18 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም ከ55 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ አባላት ወጭን በመሸፈን በተኝቶና ተመላላሽ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የማህበረሰብ ጤና መድህን ከ15 ዓመታት በፊት በ13 ወረዳዎች በሞዴል ደረጃ ተጀምሮ አሁን ላይ 1 ሺህ 279 ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።


 

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው፤ የክልሉን 90 በመቶ ማህበረሰብ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ከዚህ ውስጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 98 በመቶ የሚሆኑ አባላት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በመፈጸም መታወቂያቸውን ማደስ መቻላቸውን ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ጥራት ያለው ለማድረግ የዲጂታላይዜሽን አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ለተከታታይ 3 ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም