ቀጥታ፡

የዲጂታል መድረኮችን ተጠቅሞ እየሰፋ የመጣውን የሰዎች ሕገ-ወጥ ዝውውር ወንጀል ለመግታት ዓለም አቀፍ አጋርነት አስፈላጊ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል መድረኮችን ተጠቅሞ እየሰፋ የመጣውን የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ወንጀል ለመግታት ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ፣ የተቋማት ትብብር እና ዓለም አቀፍ አጋርነት አስፈላጊ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ። 

ሚኒስቴሩ ይህንን ያሳወቀው ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 13ኛው ዓለም አቀፍ የሰው ንግድን የመከላከል ቀን ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቸርነት ሆርዶፋ እንደገለጹት፤ በዲጂታል መድረኮች እየተስፋፋ የመጣውን የሰው ንግድ ወንጀል ለመከላከል የተጠናከረ የሕግ ማዕቀፍ፣ የተቋማት ቅንጅት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ ነው። 

በግዳጅ የሰው ሕገ-ወጥ ዝውውር ወንጀል የበርካታ ወጣቶችን ተስፋ ያጨለመ፣ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ ጭንቀት የዳረገ እና በማህበረሰቡ ላይ ተጨማሪ ጫና የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት ወንጀሉን ለመግታት የሕግ ማዕቀፎችን እያጠናከረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይም በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ዘዴዎች ሰዎችን አስገድዶ በወንጀል ላይ የሚያሰማሩ ድርጊቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በሕጉ  መካተታቸውን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም የሕግ አስከባሪ አካላትን አቅም በዲጂታል ምርመራ፣ በፋይናንስ ክትትል፣ በኤሌክትሮኒክ ማስረጃ እና በሳይበር ወንጀል ምርመራ ላይ ያለውን እውቀትና ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።


 

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ፕሮግራም ኦፊሰር ሜሞሪ ምዋሌ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ አጋቾች በሐሰተኛ የሥራ ማስታወቂያዎች እና ህገ-ወጥ መረቦች በመጠቀም በተለይም የተማሩ ወጣቶችን ያታልላሉ። 

ተጎጂዎቹ ሕጋዊ ሥራ ለማግኘት አልመው ቢሄዱም፣ በተለያዩ አገራት የማጭበርበር ማዕከላት ውስጥ ታስረው የኦንላይን ማጭበርበር ወንጀሎችን በግዳጅ እንዲፈጽሙ እንደሚደረጉ አብራርተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርት፣ የዲጂታል ክህሎት ወይም የፓስፖርት መኖር ብቻውን ከእነዚህ የተራቀቁ የሰው ሕገ-ወጥ ዝውውር መረቦች እንደማይጠብቅ ገልጸው፤ ለወጣቶች ትክክለኛ መረጃ ማድረስ፣ ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም እና የአገራትን ትብብር ማጠናከር ቀዳሚ መፍትሔዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ተጎጂዎቹ ሕጋዊ ሥራ ለማግኘት አልመው ቢሄዱም፣ በተለይም በማያናማር፣ በካምቦዲያ እና በታይላንድ በሚገኙ ዋና ዋና የማጭበርበር ማዕከላት ውስጥ ታስረው የኦንላይን ማጭበርበር ወንጀሎችን በግዳጅ እንዲፈጽሙ እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም