በዋናው የምክክር ጉባኤ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ በማስተጋባት የጋራ አሸናፊነትን ለማጎናጸፍ ገንቢና አካታች ምክክር እያደረግን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዋናው የምክክር ጉባኤ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ በማስተጋባት የጋራ አሸናፊነትን ለማጎናጸፍ ገንቢና አካታች ምክክር እያደረግን ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ በማስተጋባት የኢትዮጵያን የጋራ አሸናፊነት ለማጎናጸፍ ገንቢና አካታች ምክክር እያደረጉ እንደሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዋናው የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
በካናዳ፣ በታላቋ ብሪታኒያ እና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምክክሩ ሂደት ከአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊዎችን ከመለየት ጀምሮ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎና አካታችነት ያረጋገጠ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በዋናው የምክክር ጉባኤ እየመከረች መሆኗን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤውም ለዘመናት የቆዩ ሀገራዊ አለመግባባቶችን በሃሳብ የበላይነት በመመካከር የጋራ መግባባትን ለመገንባት ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ዶክተር ገዛኸኝ ወርዶፋ እንዳሉት፤ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ኢትዮጵያውያን በአንድ አዳራሽ ተሰባስበው ስለሀገር መምከራቸው ዘርፈ ብዙ ትርጉም አለው።
ይህም በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ምክክርን በማካሄድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክር የማይፈታ ችግር የለም ያሉት ዶክተር ገዛኸኝ፤ በዋናው የምክክር ጉባኤ ሂደትም ለኢትዮጵያ የሚበጁ ወሳኝ ሃሳቦችን በማንሸራሸር የሚመከርበትን ዕድል የፈጠረ ታላቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
በዚህም በመከባበር መንፈስ አንዱ የአንዱን ሃሳብ እንዲገነዘብ በማስቻል የጋራ አሸናፊነትን በሚያጎናጽፉ አጀንዳዎች ላይ ገንቢ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዋናው የምክክር ጉባኤም ከኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ባሻገር ለአፍሪካውያን ጭምር አርዓያ የሚሆኑ የጋራ መግባባት ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡበት እንደሚሆንም እምነታቸውን ጠቅሰዋል።
በታላቋ ብሪታኒያ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ሔለን በፍቃዱ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በእርግጥም ለዘመናት በቆዩ ችግሮቿ ላይ የጋራ መፍትሔ ለማበጀት እየመከረች ነው ብለዋል።
በጉባኤውም በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ነፃና አካታች ምክክር እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዋናው የምክክር ጉባኤ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን በማጎልበት የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ገንቢ ምክክር እያካሄዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በተመካካሪዎች መካከል በሕዝብ ጥያቄዎች ላይ የጋራ አረዳድና መግባባት የሚፈጥር ነፃና ግልጽ ምክክር እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም።
የጉባኤው አንድነትን በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ መልካም አሻራ ለማስቀመጥ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ያሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ገዛኸኝ ሱማሞ ናቸው።
በተመካካሪዎች መካከል የሚንጸባረቀው የምክክር መንፈስ የአንዱ ህመምም ሆነ ደስታ የጋራ መሆኑን በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።
በዚህም የምክክሩ አሳታፊነትና አካታችነት የኢትዮጵያን የጋራ አሸናፊነት በማጎናጸፍ ለአፍሪካውያን ጭምር ተምሳሌት የሆነ ምክክር እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪ ከድጃ መሐመድ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉባኤው በሕዝብ ስብጥር አካታችና አሳታፊነት ጎልቶ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ ከአራቱም ማዕዘናት የተሰባሰቡ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች የዘመናት አጀንዳዎች ላይ በመምከር የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስችል እምነታቸውን ተናግረዋል።
የምክክር ጉባኤው የአንድ ወገን ሃሳብ የሚቀርብበት መድረክ አይደለም፤ ይልቁንም የጋራ አሸናፊነትን በማጎናጸፍ የኢትዮጵያን የተሻለ መጻኢ ዕድል መገንባት የሚያስችል የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱም ከአጀንዳ ማሰባስብና ተሳታፊ ልየታ ጀምሮ እስከ ዋናው የምክክር ጉባኤ ድረስ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ የሚመክሩበትን አሳታፊና አካታች ዕድል እንደተፈጠረም ጠቁመዋል።