ቀጥታ፡

በ2018 በጀት ዓመት በመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ከ597 ቢሊየን ብር በላይ ግዥ ተፈጽሟል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ከ597 ቢሊየን ብር በላይ የተጠናቀቀ ግዥ መፈጸሙን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ገለጸ።

ባለሥልጣኑ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አፈጻጸምና የ2019 ዕቅድ ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር እያደረገ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ በዚህ ወቅት፤ ባለሥልጣኑ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን፣ የንብረት አስተዳደርንና አወጋገድ ሂደትን በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት በማስተዳደር ለዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግር ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 172 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና 196 ቅርንጫፍ ተቋማቶቻቸው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን መጠቀማቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ሥርዓት ተመዝግበው ምርትና አገልግሎት የሚያቀርቡ ተቋማት ቁጥርም ከ135 ሺህ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገለት ለአጠቃቀም ምቹ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ከ597 ቢሊየን ብር በላይ ግዥ መፈጸሙን አስታውቀዋል።


 

የግዥ ሥርዓቱ ከፌዴራል ተቋማት ባለፈ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል።

በሌሎች ክልሎችም የሥርዓቱን መሠረተ ልማት ለማስፋፋት በስልጠናና በአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለሥልጣኑ ከኤሌክትሮኒክ ግዥ ባሻገር የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴና የነዳጅ አጠቃቀም መቆጣጠር የሚያስችል ''e-Fleet Management'' ሥርዓት ወደ ሥራ ማስገባቱንም ገልጸዋል።

በዚህም 139 ተቋማት ሥርዓቱን ለመጠቀም መግባታቸውንና 69 ተቋማት ከ7 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን መረጃ መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በ2019 በጀት ዓመትም ሁሉም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ውጤቶች የአገልግሎት አሰጣጡን ማቀላጠፍና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር የሚያስችል የዲጂታል ሽግግር እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም