ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገረ-መንግስት ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚያኖር ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገረ-መንግስትና ለፖለቲካ ባህል ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በኮሚሽኑ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ምእራፍ ላይ ይገኛል።

የምክክር ሂደቱን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ምክክሩ በምክክር የምትጸና እና ለዜጎች ሁሉ የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ እድል መሆኑን አንስተዋል።

አካታችና አሳታፊ በሆነው የምክክር ሂደት በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ነፃና ጥልቅ የሆነ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ተገንዝበናል ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ፤ ውጤቱ የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች ማከም ያስችለናል ብለዋል። 

በምክክሩ ጉባዔው አጀንዳዎችን በጥንቃቄ በመለየት ነፃና ጥልቅ የሆነ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ተገንዝበናል ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ፤ በምክክር ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለመሻት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ባሻገር በተለይም ለሀገረ-መንግስት ግንባታና ለአዲስ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚያኖር ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ሀገራት ያጋጠሟቸውን ችግሮች በምክክር መፍታታቸውን የጠቆሙት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያም በተደራጀና በተሻለ የምክክር ሂደት ለሌሎች ሀገሮች በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች ብለዋል።

ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ የዜጎች መተማመን፣ ሰላም እና ደህንነትን  ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት  ብርሀኑ (ዶ/ር)  ሀገራዊ  ምክክሩም  ይህን ለማረጋገጥና  ለቀጣይም  ልምድ የሚወሰድበት  ይሆናል ብለዋል።

ለዚህም  ዜጎች በየደረጃው ተወያይተው አጀንዳቸውን  ማቅረባቸው እና ለተግባራዊነቱ በወከሏቸው ሰዎች አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የምክክር ጉባኤ ውጤቱን ሁላችንም የምንጠብቀው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ለዘላቂ እድገት፣ ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ እና ለህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነት መጎልበት በጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም