ቀጥታ፡

የአካባቢ ፀጋን በማወቅ የተገኘ ስኬት-የምህንድስና ምሩቁ ሞዴል አርሶአደር

የምህንድስና ምሩቁ ሞዴል አርሶአደር

(በቀደሰ ተክሌ- ሚዛን አማን)

እውቀት በቅድሚያ ራስን ለመለወጥ ከዚያም አልፎ ለሀገር ሲተርፍ ይበልጥ ትርጉም ይሰጣል። ማወቅ ከተማርነው ትምህርት የዘለለ መረዳት እንዲኖረን በማድረግ ለነገሮች ያለንን የእይታ አድማስ ያሰፋል። የ"ለምን?" ጥያቄዎችን በማንሳት በምላሹ መፍትሔ ለመስጠት ይሞክራል። በዚህም ረገድ ከተማሩበት ትምህርት ባሻገር ሌላ ዓለም እንዳለ በማሳየት በኩል ተምሳሌት የሚሆኑ አሉ። የዚህ ፅሁፍ ባለታሪክም ከምህንድስና ትምህርቱ ባሻገር ያለውን ፀጋ በእርጋታ ተመልክቶ ውጤታማ መሆን እንዴት እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ የሆነ ወጣት ነው። 

ወጣቱ ኢንጂነር ይንገሥ ጌታቸው ይባላል። በሸካ ዞን የኪ ወረዳ የአላሞ ቀበሌ ነዋሪ ነው። በአካባቢው ባከናወነው ውጤታማ የግብርና ሥራ ሞዴል አርሶ አደር የሚል ሌላ የማዕረግ ስያሜን አግኝቷል። ይንገስ አስተዳደጉ በግብርና ስራ ከተሰማሩ ቤተሰቦቹ የእርሻ ማሳ ጋር የተያያዘ ነው። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከትምህርት ቤት መልስ ቤተሰቦቹን በግብርና ስራ ያግዛል። ይህም የእርሻ ሥራን በአግባቡ እንዲረዳ አድርጎታል። ቤተሰቦቹን የሚያግዝበት እጁ የሻከረ ጉልበቱ የበረታ ነበር።


 

ከዚያ አለፍ ሲልም በትምህርቱ ጎበዝ ስለነበርም እስከ ዩኒቨርሲቲ ዘለቀ። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርቱን አጠናቆ ተመረቀ። ወደ ቀዬው ሲመለስም ስራ ከመፈለግ ይልቅ ከልጅነቱ ጀምሮ በሚያውቀው የግብርና ስራ ላይ ለመሰማራት በመወሰን በአጭር ታጥቆ ወደ ስራ ገባ። ለዘመናት ውጤታማ ሳይሆን የቆየውን የእርሻ ስራ ወደ የተሻለ ደረጃ ላይ የማድረስ ራዕይን ሰንቆ እጁን ከጭቃ ጋር አገናኘ።

ወጣት ይንገስ ወደ እርሻ ስራ ለምን እንደመጣ ሲናገር "ቤተሰቦቼ ዕድሜያቸውን ሙሉ በግብርና ሥራ ነው የቆዩት፤ ነገር ግን ለውጥ የሚባል ነገር የለም።" ይህ ቁጭት ነው እንግዲህ "ለምን?" የሚል የመብሰልሰል ጥያቄን ሊያጭርበት የቻለው። የዘልማድ አሰራር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የግብዓት አጠቃቀም፣ በዕውቀት ያለመመራትና ሌሎች ምክንያቶች የእርሻ ስራውን ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረጉት ተገነዘበ።  ለዚህም ክፍተትን ማየት፣ መንስኤ መለየት፣ ከዛም ለውጥን አልሞ ወደ ውጤት መቀየር መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ተረዳ። በትናንቱ መንገድ ባለመጓዝ የዘመነና ገበያው የሚፈልገውን ምርት ለማምረት ለራሱ ቃል ገባ፤ ከራሱ ጋር ተስማማ።


 

ወጣቱ አካባቢው ለቅመማ ቅመም ምርት የተመቸ ፀጋን የታደለ መሆኑን ስለሚያውቅ ይህን ዕድል ለመጠቀም በማሰብ ውድ የሆኑ የቅመማ ቅመም ምርቶችን በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ወጠነ። ወጥኖም አልቀረም ወደ ተግባር ለመቀየር ተንቀሳቀሰ። ይህን ጊዜ ነው የሕይወቱ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው። ከአላሞ ተነስቶ ወደ ቴፒ የግብርና ምርምር ማዕከል አቀና። ማዕከሉ በብሔራዊ ደረጃ በቅመማ ቅመም ላይ ትኩረት በማድረግ የምርምር ስራዎችን ይሰራል። የምርምር ማዕከሉ ከሚያወጣቸው ዝርያዎች መካከል ቫኒላ አንዱ ነው። ቫኒላ ደግሞ በዓለማችን ውዱ ቅመም ነው።

ወጣቱ ይንገስም ፍላጎቱ ተሳክቶ ዝርያውን ከማዕከሉ በመውሰድ ማሳው ላይ ተክሎ መንከባከብ ጀመረ። የቫኒላ የአመራረት ሂደት ትዕግሥትን የሚጠይቅ ነው። በተለይ ፍሬ እንዲሰጥ እርስ በእርስ የማዳቀሉ ተግባር ጥብቅ ክትትልና ትጋትን የሚጠይቅ ነው። ሂደቱን ተሻግሮ ምርት እስከሚሰጥ ድረስ ወጣቱ ከባለሙያዎች ድጋፍን ከመጠየቅ ባሻገር ድረ-ገፅን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቫኒላ አመራረት ያለበትን ደረጃ እስከ መከታተል የደረሱ ጥረቶችን ያደርጋል። በዚህም ብዙዎች ተስፋ የቆረጡበትን የቫኒላ ቅመም ምርት እርሱ በአግባቡ አልምቶ ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል። እነሆ አሁን ላይ ወጣቱ ካፒታሉን በማሳደግ በየዓመቱ ሚሊዮን ብሮችን ወደ ካዝናው የሚያስገባ ባለሃብት ሆኗል። 

በተጨማሪም ወጣቱ የቤተሰቡን ማሳ በአዲስ የቡና ዝርያ ለመሸፈን በሳይንስ የተደገፈ የማሳ ዝግጅት አድርጎ ቡና መትከል ጀመረ። እነሆ ዛሬ 5 ሄክታር በምርምር የተገኘ ምርጥ የቡና ዝርያ ለምቶ ፍሬ መስጠት ጀምሯል። ይህ የቡና ውጤታማነት ዝቅተኛ መልክዓ-ምድር ባላት የአላሞ ቀበሌ ከዚህ ቀደም የማይታሰብ አዲስ ብሥራት ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ የቡና ዝርያዎች ለቆላማ አካባቢ ተስማሚ ስላልነበሩ አርሶአደሮች  ቡና አልምተው ብዙም ተጠቃሚ አይሆኑም ነበር።

ወጣቱ የቴፒ ግብርና ምርምር ያወጣቸውን እንደ "K-1፣ K-2 እና I-3" በሚል ስያሜ የሚታወቁ የቡና ዝርያዎችን በመውሰድ በማሳው ላይ በመሞከር ውጤት አምጥቶለት ችግኞቹ በ9 ወር አብበው የምሥራች ፍሬ ሊሰጡ ችለዋል። ዝርያዎቹ በሙሉ አቅም ምርት ሲሰጡ በሄክታር ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰብባቸዋል። ኢንጂነሩ ሞዴል አርሶ አደር በቫኒላ እና በቡና ልማት ላይ ብቻም ራሱን አልገታም። በአቮካዶ፣ በሙዝ፣ በአናናስ፣ በፓፓያና በሌሎች የፍራፍሬ ዓይነቶችን ጨምሮ በካካዎ እና በቁንዶ በርበሬ ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ በመሰማራትም ተጠቃሚ መሆን ችሏል። የካካዎን ምርት ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲውል በማድረግ የውጭ ምንዛሬን የማዳን ዓላማን ይዞ ወደ ምርት መግባቱን ይናገራል። ካካዎ ቾኮሌት ለሚያመርት ፋብሪካ በግብዓትነቱ ተጠቃሽ ነው። 


 

ወጣት ይንገስ በተለያዩ ምርቶች ላይ ከመሰማራት ባሻገር የተሻሻሉ የዘር ችግኞችን እያባዛ ለአካባቢው አርሶ አደሮችም እያቀረበ ይገኛል። በዚህም በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ በማግኘት ራሱን እና ቤተሰቡን የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ አድርሷል። የሸካ ምድር ፍሬ ለመስጠት የምርት ዓይነት አይመርጥም። የሰጡትን ያበቅላል፤ ይህ ደግሞ በተፈጥሮ የተቸረ ጸጋ ነው። የወጣት ይንገሥ ማሳ አንድ ምርት ብቻን የማልማት ዕድልን ማን ይሰጠዋል። በጥምር የእርሻ ስነ-ዘዴ እርስ በእርስ ተመጋጋቢ የሆኑ የተለያዩ ምርቶች በአንድ ላይ ይመረታሉ።

ለአብነትም አቮካዶ፣ ፓፓያና ሙዝ በአንድ ላይ ይመረታሉ። ይህም ውጤታማ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓትን ፈጥሯል። ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር ጥበቃ፣ ለጥላና የእንጨት ሥራ ውጤቶች ግብዓት የሚሆነው የግራቪላ ዛፍ ለቁንዶ በርበሬ ልማት መሠረት ሆኖ ያገለግላል። መንግሥት "ምግቤን ከጓሮዬ" በሚል ያስጀመረው ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ማሳያ ከሆኑ ማሳዎች ውስጥ የሚመደበው የወጣቱ ማሳ ከፋብሪካ ውጤቶች በቀር ይህ ጎደለ የሚባልለት አይደለም። ከወተት እስከ ማር፣ ከአትክልት እስከ አዝርዕት ሁሉም በመጠኑ ይመረታል።

ውጤታማ የግብርና ሥራ መሬትን አርሶ ከዘር ጋር ከማገናኘት ያለፈ ትርጉም የሚፈልግ መሆኑን ከኢንጂነሩ ሞዴል አርሶ አደር ይንገሥ የሥራ ተሞክሮ መማር ይቻላል። በቴክኖሎጂ ዘመን ከቴክኖሎጂ ርቆ ማልማት ድካም ከማብዛት ውጭ ውጤቱ አርኪ አይደለም። የግብርና ምርቶችን በከፊል ማቀነባበር የሚችሉ ማሽኖችን በመትከል ምርቶቹን በጥራት ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሷል።

ከወጣት ይንገሥ የሥራ ውጤታማነት በኋላ ብዙዎች የአካባቢው ወጣቶች ተነቃቅተዋል። ብዙ ዓመት ሰፊ ማሳ አልምተው ጥቂት ምርት ይሰበስቡ የነበሩ አርሶ አደሮችም ወደ ይንገሥ ማሳ ጎራ ብለው ተሞክሮ በመቅሰም ለትግበራው ወደ ማሳቸው አቅንተዋል። ተሞክሮውን ፈጥነው ወደ ውጤት ከቀየሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ብርሃኑ ጌታቸው አንዱ ነው። እርሱም ዛሬ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘ የ5 ሄክታር ቡና ማሳ ባለቤት ሆኗል። ቡናን ከመትከል በተጨማሪ ዘር በማፍሰስ ችግኝ የማዘጋጀት ተግባር እንደሚያከናውን ገልጿል።


 

አርሶ አደር ታደሰ እጅጉ፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት በእርሻ ሥራ ቢቆዩም ውጤታማውን መንገድ ሳይከተሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። አሁን ላይ ወጣቶቹ ሠርተው ባመጡት ውጤት ተደስተው አሠራሩን በማሳቸው ለመተግበር መነሳሳታቸውን ገልጸዋል። ያላቸውን 10 ሄክታር የእርሻ ማሳ ከልጆቻቸው ጋር በማልማት በአዳዲስ የቡና፣ የቅመማ ቅመም እና የፍራፍሬ ልማት ለመሸፈን ማቀዳቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ተስፋዬ ግዛው የየኪ ወረዳ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽሕፈት ቤት ባለሙያ ናቸው። በወጣት ይንገሥ ጌታቸው የተከናወነው ውጤታማ ሥራ የወረዳውን የግብርና ሥራ ያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል። በቡና ምርታማነት ላይ የታየው ተሞክሮ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች እንዲስፋፋ እያደረግን ነው ብለዋል።


 

በተለይ በጥምር እርሻ አመራረት ሥነ-ዘዴ የታየው የቅመማ ቅመም እና ፍራፍሬ ማሳ ውጤት በጠባብ ማሳ ብዙ የምርት መጠን መሰብሰብ የሚቻልበትን መንገድ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። የኢንጂነሪንግ ምሩቁ ወጣት ተሞክሮ የአካባቢን ፀጋ ባለመመልከት በሥራ ፍለጋ ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ወጣቶች የሚያስተምረው ዘርፈ ብዙ ትምህርት አለ ብለዋል። 

የሰው ልጅ ሕይወት የሚቀየረው በሥራ ዓይነት ሳይሆን በጠንካራ የሥራ ባህል ነው። በእጅ ያለን ወርቅ እንደ መዳብ ቆጥሮ የሩቅ ከመሻት ይልቅ በአጠገብ ያለን ጸጋ አይቶ ወደ ውጤት መቀየር ነገን በተሻለ ደረጃ አሻግረን እንድናይ ያስችለናል። ለዚህ ደግሞ የኢንጂነሪንግ ምሩቁ ሞዴል አርሶ አደር ይንገሥ ጌታቸው ተግባር ሕያው ምስክር ነው። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም