ኢኒስቲትዩቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራዎችን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢኒስቲትዩቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራዎችን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦ ኢኒስቲትዩቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራዎችን እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የኢኒስቲትዩቱ አመራር አባላት እና ሰራተኞች "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሃይቅ ዳርቻ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢኒስቲትዩት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራዎችን ያጠናክራል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን እያስገኘ መሆኑንም አክለዋል።
በዚህም የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በሰፊው እየተተከሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በመከላከል አረንጓዴ ዐሻራ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸው፤ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ታሪክ እየቀየረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩትም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ ችግኝ በመትከል በቀጥታ ከመሳተፍ ባለፈ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
የ2018 ዓም አረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬታማ እንዲሆን ኢኒስቲትዩቱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም ጥናት በማድረግ በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ ላይም ኢኒስቲትዩቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢኒስቲትዩቱ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክተር ፍቃዱ በዳዳ በበኩላቸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ እየተመዘገበ ያለው ውጤት የበለጠ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ላለፉት ዓመታት ዐሻራቸውን ማኖራቸውን አስታውሰው፤ ዛሬ የምናኖረው ዐሻራ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ችግኞችን መትከል አንዱ ግብ ቢሆንም ተንከባክቦ ለጽድቀት ማብቃት፤ ከሁላችን ይጠበቃል ያለችው ደግሞ የኢኒስቲትዩቱ ሰራተኛ ወጣት ቤዛዊት ወንድምአገኝ ናት።