ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጤና ተቋማትን በማስፋፋት የአገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ ተችሏል

ሸገር፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በሸገር ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጤና ተቋማትን በማስፋፋት የአገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ መቻሉን የከተማው ጤና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከያዛቸው ዋና ዋና  ግቦች አንዱ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ጥራት ማረጋገጥ ነው። 

ይህም የአካባቢውን ማኅበረሰብ የመሠረተ-ልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ፍላጎት በተለይም ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ጥያቄን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበራ ቦቶሬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በከተማው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በከተማው በ12ቱ ክፍለ ከተሞች አዳዲስ የጤና ተቋማትን በመገንባት፣ ነባር ተቋማትን በማስፋፋትና ደረጃቸውን በማሻሻል፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና የሰው ኃይልን በማሟላት፣መሠረታዊ ሕክምናዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ 12 የጤና ኬላዎች፣ 1 የጤና ጣቢያ፣ እንዲሁም 2 ጠቅላላ ሆስፒታሎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል በተሠሩ ሥራዎች የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም በከተማው በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ 11 ብሎኮች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የተገነቡት ተጨማሪ ብሎኮች የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

በተጨማሪም የጤና አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ረገድ የሕክምና መሣሪያዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት በተደረጉ ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች ውስጥ የጤና ቁሳቁሶች ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።


 

በዚህ ረገድ በበጀት ዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥት በጀትና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን ለጤና ተቋማት ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

የሰው ኃይል ከማሟላት አንጻርም ከ400 በላይ የጤና ባለሙያዎች በቅጥርና በዝውውር ወደ ጤና ተቋማቱ እንዲገቡ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በሸገር ከተማ ከዚህ ቀደም 39 በመቶ የነበረውን የጤና ጣቢያዎች ሽፋን በበጀት ዓመቱ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ሃላፊው  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም