ሀገራዊ መግባባት ሊያመጡ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ያለ ምንም ገደብ እየመከርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ መግባባት ሊያመጡ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ያለ ምንም ገደብ እየመከርን ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ሀገራዊ መግባባት ሊያመጡ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ያለ ምንም ገደብ እየመከርን ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል።
ተመካካሪ አቶ መሐመድ አሚን መሀዲ ፤ በምክክሩ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተካተቱ መሆኑን ጠቅሰው በነፃነትና በእኩልነት እየመከሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተመካካሪዎች ሀገርን ሊገነቡ፣ ሊያጠናክሩና ሀገራዊ መግባባት ሊያመጡ የሚችሉ ሃሳቦችን ያለ ምንም ገደብ በነፃነት እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በሂደቱ የእያንዳንዱ ወገን ድምፅና ሀሳብ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው በመሆኑ፣ ይህ የጋራ ምክክር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መግባባትን ለመፍጠር አዎንታዊ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
መድረኩ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል አስተማማኝ መሰረት እንደሚጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሂደቱ ሀገሪቱን ወደ ዘላቂ ሰላምና የልማት ምዕራፍ ለማሸጋገር ታላቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ተመካካሪ አቶ ግዛው ከበደ እንዳሉትም፤ ምክክሩ ከአነስተኛ ቡድኖች ጀምሮ በደረጃ ሁሉንም አመለካከቶችን በማካተት በስኬታማነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ በተሰጡ አጀንዳዎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል።
ሂደቱ በኮሚሽኑ አሰራር መሰረት ያለ ምንም ተፅዕኖ እየተካሄደ በመሆኑ፣ ምክክሩ አማራጭ የሌለው አቋምና የመፍትሔ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።
ተመካካሪ ነብይ ምህረቱ አዳነ በበኩላቸው፤ የምክክሩ ሂደት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመካካሪዎች ለሀገር የሚበጁ መፍትሔዎችን በጋራ እየቀረጹ ይገኛሉ ያሉት ነብይ ምህረቱ፣ ምክክሩ በመቀራረብ የመተማመንና የአብሮነት መንፈስን እያጠናከሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሂደቱ በህዝቦች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይዞ እንደሚመጣ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል።