ቀጥታ፡

አገልግሎቱ የውጭ ባለሀብቶች በሚሰማሩባቸው የትኛውም የሥራ መስኮች አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ምህዳር እንዲፈጠር የሚያግዝ ስምሪት እያከናወነ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውጭ ባለሀብቶች በሚሰማሩባቸው የትኛውም የሥራ መስኮች አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ምህዳር እንዲፈጠር የሚያግዝ ስምሪት እያከናወነ እንደሚገኝ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) የአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል ከተመራ ልዑክ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለሌሎችም የውጭ ባለሀብቶች ለሚሰማሩባቸው የትኛውም የሥራ መስኮች አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ምህዳር እንዲፈጠር የሚያግዝ ስምሪት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ይህም ለአሜሪካ የቢዝነስ ማኅበረሰብ መተማመን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በየጊዜው ሲያጋጥሙ የነበሩ የፀጥታ ስጋቶችን በማስወገድ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ደኅንነትንና ሰላምን የማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ቀጣናዊ መረጋጋት ለማስፈን የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረጉ ስትራቴጂዎች በመንደፍና ቁርጠኛ አቋም በመያዝ እየተገበረ መሆኑን ገልጸው፤ የመረጃና ደኅንነት ተቋሙም በዚህ በኩል ያለውን ዝግጁነት ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል የአሜሪካ ኩባንያዎች በሀገሪቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ እንደሰጡና ለዚህም አስቻይ ሁኔታዎች መኖሩን እንደገለፁ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም