የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ነው - ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ነው - ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ነው ሲሉ ተመካካሪ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ ገለጹ።
ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል።
ተመካካሪ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው የህዝብንና የሀገርን ጥያቄዎች ያለአንዳች ተጽዕኖ በነፃነት ተመካክሮ የጋራ መፍትሔ የሚሰጥበት ታላቅ መድረክ ነው።
የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽና ውክልና የያዙት አራት ሺህ ተመካካሪዎች በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሰፊ ዕድል ያገኘንበት ነውም ብለዋል።
የህዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በኃይል ሳይሆን በሰለጠነና በሰላማዊ ምክክር ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው የሚመካከሩ የህዝብ ወኪል ተማካካሪዎችም ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ እየተመካከሩ የመፍታት ጠንካራ እምነት እያዳበሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
ከምክክር ውጪ የሚደረግ የኃይል አካሄድ የህዝብን ስቃይ ከማባባስ ውጭ አንዳችም ፋይዳ እንደማይኖረው አስረድተዋል።
በጉባኤው የሚመከርባቸው አጀንዳዎች የግለሰብና የቡድን ሳይሆኑ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ የጋራ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም የሀገር መሰረታዊ ችግሮች መፍትሔ አግኝተው መግባባት ሲፈጠርባቸው የሁሉም ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እያገኘ እንደሚሄድ አብራርተዋል።
የምክክር ሂደቱ በጥሩ መግባባትና በመልካም መንፈስ እየተመራ መሆኑን የጠቀሱት ኮሎኔል ፈንታው፤ በምክክር ጉባኤውም ከሀገርና ከህዝብ በላይ ሊበልጥ የሚችል ጉዳይ እንደሌለ እየታየ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ተመካካሪዎች የግለሰብን እና የቡድን ጠባብ ፍላጎቶችን በመተው ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ሲሉ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን ባለው የሰመረ የምክክር መንፈስ ለሀገር እና ለህዝብ የሚበጀው ትክክለኛ የጋራ ውሳኔ እንደሚተላለፍ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ሂደትም ፍሬ አፍርቶ የተሻለችና የፀናች ሀገርን በእርግጠኝነት እውን እንደሚያደርግ ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።